በክልሉ በ53 ሺህ ሄክታር ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ እንደሚከናወን ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በቤኒሻንጉል ጉመዝ ክልል በ53 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ እንደሚከናወን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል፡፡
በቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ዘርፍ ም/ሃላፊ አቶ አብዱልከሪም ሙሳ እንዳሉት÷ በዘንድሮ በጋ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለማከናወን የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል።
የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ የአካባቢ ምህዳርን ለማስጠበቅ እና የአፈር ለምነትን ለማሻሻል ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ የፊታችን ጥር አጋማሽ በሚጀመረው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ 53 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት መታቀዱን አንስተዋል፡፡
በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራውን በስኬት ለማከናወን ለግብርና ባለሙያዎች እና ቀያሽ አርሶ አደሮች ሥልጠና መሰጠቱን ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ 247 ሺህ ዜጎች እንደሚሳተፉ ጠቁመው÷ ለሥራው የሚውሉ የቁፋሮና ሌሎች መሳሪያዎች መዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ የሚከናወንባቸው 429 በላይ ተፋሰሶች መለየታቸውንም ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት፡፡
በአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራው የክልሉ ሕዝብ እና የሚመለከታቸው አካላት በንቃት እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ