የካፒታል ገበያ ለግሉ ዘርፍ መጠናከርና ለማይበገር ኢኮኖሚ ግንባታ ጉልህ አበርክቶ እንዳለው ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የካፒታል ገበያ ለግሉ ዘርፍ መጠናከርና ለማይበገር ኢኮኖሚ ግንባታ ጉልህ አበርክቶ እንዳለው የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀና ተኸልቁ ገለጹ።
ዋና ዳይሬክተሯ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም አዘጋጅነት በሚቀርበው ”ኢትዮጵያ ኢን ፎከስ” ፕሮግራም ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም÷ ካፒታል ገበያ የፋይናንስ አካታችነት፣ ለሁሉን አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያ ውጤታማነት፣ ዘላቂ የፋይናንስ አማራጭ ለመፍጠርና የሀብት ምንጮችን ለማስፋት ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
በኢኮኖሚ ሪፎርሙ መሰረት የተቋቋመው የካፒታል ገበያ ለግሉ ዘርፍ መጠናከርና ለማይበገር ኢኮኖሚ ግንባታ ጉልህ አበርክቶ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡
ጠንካራ የካፒታል ገበያ ስርዓት ለመገንባት ደግሞ ጠንካራ ተቆጣጣሪ አካል፣ ተአማኒ የገበያ አገናኝ፣ ቴክኖሎጂ፣ አስቻይ ማዕቀፍና ዘርፉን በብዝሃ የአክሲዮን ባለቤትነት የሚመራ ማድረግ ይጠይቃል ብለዋል።
በዚህም መንግስት የካፒታል ገበያ ሲፈቅድ አስቻይ የሕግ ማዕቀፍና ዘርፉን የሚመራውን የካፒታል ገበያ ባለስልጣን እንዲቋቋም ማድረጉን አውስተዋል።
ባለስልጣኑ በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሰረት በመንግስትና በግል ዘርፍ ትብብር በአክሲዮን ኩባንያነት ለተቋቋመው የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ የተለያዩ ሰነደ ሙዓለ ነዋዮችን ያገበያይ ዘንድ ፈቃድ መስጠቱን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በቅርቡ ስራ እንደሚጀምርም መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡
በዘርፉ ለሚሰማሩ ዓለም አቀፍ ተዋንያን በግልም ሆነ በሽርክና የሚሰማሩበት አሰራር የማመቻቸት፣ ፈቃድ የመስጠትና ወቅታዊ መረጃዎችን ተደራሽ የማድረግ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡