Fana: At a Speed of Life!

ከኢትዮጵያ ጋር ገናን የሚያከብሩ ሀገራት እነማን ናቸው?

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 29፣2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት (የገና በዓል) በክርስቲያኖች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩት በዓላት በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡

በፈረንጆቹ የዘመን አቆጣጠር የሚጠቀሙ ሀገራት ገናን ከሁለት ሳምንታት ቀደም ብለው ታሕሣሥ 25 ቀን 2025 ላይ ያከበሩ ሲሆን÷ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ሀገራት ደግሞ ገናን ዛሬ እያከበሩ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል በአብዛኛው ታሕሣሥ 29 የሚከበር ቢሆንም÷ በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ታሕሣሥ 28 ላይ እንደሚከበር መገንዘብ ይገባል፡፡

በመሆኑም ዛሬ ገናን ከኢትዮጵያ ጋር በተመሳሳይ ዕለት እያከበሩ ከሚገኙት መካከል÷ የኤርትራ እና የግብፅ የክርስትና እምነት ተከታዮች ይገኙበታል፡፡

በተጨማሪም የሩሲያ፣ ዩክሬን፣ ቤላሩስ፣ ጆርጂያ፣ ካዛኪስታን፣ ሞልዶቫ፣ ሰርቢያ፣ ሞንቴኔግሮ፣ ቡልጋሪያ እና ሜቄዶኒያ ክርስቲያኖች ገናን ከኢትዮጵያ ጋር በተመሳሳይ ጊዜ ያከብራሉ፡፡

በዓሉ በሐይማኖታዊ ሥርዓቶች እና እንደየሀገራቱ ባሕል ከምግብ እና መጠጥ ጋር በተያያዘ በተለያዩ ክንውኖች ይከበራል፡፡

ለአብነትም በኢትዮጵያ በዓሉን በሐይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓት፣ የተቸገሩትን በመደገፍ እና ስጦታ በመቀያየር ማክበር የተለመደ ነው፡፡

በዩክሬን ደግሞ ከአንድ ቤት ወደ ሌላ ቤት እየተዘዋወሩ በመጫወትና በመዝናናት ሲያከብሩ÷ በሩሲያ በ12ቱ ሃዋርያት ተምሳሌትነት በሚል በቀን 12 ዓይነት ምግቦችን እየተመገቡ ያከብራሉ፡፡

እንዲሁም ሰርቢያዊያን እሳት በማቀጣጠል ዙሪያውን ከብበው እራት እየበሉ እና እጠጡ ያከብራሉ፤ በሌላ በኩል ጆርጂያውያን በመንገዶች ላይ ሰብሰብ ብለው በመብላት እና በመጠጣት እየተጨዋወቱ በዓሉን ያሳልፋሉ፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.