ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ ማዕድ አጋሩ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ ማዕድ አጋርተዋል፡፡
የማዕድ ማጋራት መርሐ-ግብሩ በብሔራዊ ቤተመንግሥት የተከናወነ ሲሆን÷ ከአዲስ አበባ ከተለያዩ ከፍለ ከተሞች የተውጣጡ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ተሳትፈዋል፡፡
ከመርሐ-ግብሩ በኋላም የብሔራዊ ቤተ-መንግሥት ሙዚየምን መጎብኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያከናወኑት በጎ ተግባር ልዩ ደስታ እንደፈጠረላቸው በዚሁ ወቅትም የማዕድ ማጋራቱ ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡
እርስ በርስ መደጋገፍ የኢትዮጵያውያን መገለጫና እሴት መሆኑን ጠቅሰው÷ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓሉን ከአረጋውያን እና አቅመ ደካሞች ጋር ማሳለፋቸው ሁሉም በየአካባቢው ሊተገብረው ይገባል ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአቅመ ደካሞችና አረጋውያን በየጊዜው ማዕድ ከማጋራት በተጓዳኝ በልማት ስራዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለሚያከናውኑት ስራም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በተለይ የልማት ስራዎች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ መንግስት እያከናወነ ያለውን ስራም አድንቀዋል፡፡
የብሔራዊ ቤተመንግሥት ሙዚየምንም በመጎብኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸው÷ ሙዚየሙ የያዛቸው ታሪካዊ ቅርሶች አጠቃላይ ገጽታ እጅግ ማራኪ መሆኑን አንስተዋል፡፡