ላሊበላ የኢትዮጵያውያንን ጥበብ፣ ራዕይና ጥንካሬ ያሳየ ድንቅ ስፍራ ነው – ሰላማዊት ካሳ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ የላላቢላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እድሳት አካል የሆነውን የዘላቂ ላሊበላ ፕሮጀክት ጎብኝተዋል፡፡
ሚኒስትሯ በጉብኝታቸው የውቅር አብያተ ክርስቲያናቱ እድሳትና የጥገና ሥራዎች በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቱ አብያተ ክርስቲያናቱን ለመጠገንና ለመጠበቅ እንዲሁም አካባቢውን ለእንቅስቃሴ ምቹ ለማድረግ የሚያስችሉ ዋና ዋና ሥራዎችን እንዳካተተ አንስተዋል፡፡
አስቸኳይ ጥገና የሚሹ 22 ቅርሶችን መጠገንን ጨምሮ የታሪካዊ መሬት አቀማመጥ ሥራዎች፣ የአቅም ግንባታ፣ የኤግዚቢሽንና ማስታወቂያ ሥራዎች እንዳሉትም አመላክተዋል፡፡
ሁለተኛውን ዙር የጥገና ሥራ “ኢትዮጵያን ሄሪቴጅ ፕሮጀክት” ለማስጀመር ከፈረንሳይ መንግሥት ጋር ስምምነት መፈረሙን ጠቅሰዋል፡፡
ከሀገር ውስጥ እና ከመላው ዓለም በርካቶችን የምትሰበስው ላሊበላ በገና ዋዜማ በአማኞችና በጎብኚዎች ደምቃ እንደምትገኝም ሚኒስትሯ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አውስተዋል፡፡