የፈረንሳይ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ከሙአመር ጋዳፊ ገንዘብ በመቀበል ወንጀል ተከሰሱ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፈረንሳይ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ሳርኮዚ ከሊቢያ የቀድሞ መሪ ሙአመር ጋዳፊ ለምርጫ ቅስቀሳ 50 ሚሊየን ዩሮ ገንዘብ ተቀብለው ነበር የሚል ክስ ቀርቦባቸው ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ።
ፈረንሳይን ከፈረንጆቹ 2007 እስከ 2012 በፕሬዚዳንትነት የመሩት ሳርኮዚ ከሊቢያው የቀድሞ መሪ ገንዘቡን የተቀበሉት ለጋዳፊ ዓለም አቀፍ ተቀባይነትና ገፅታ ግንባታ ድጋፍ ለማድረግ እንደሆነ ተመላክቷል።
የ69 ዓመቱ ሳርኮዚ ዛሬ ፓሪስ በሚገኝ ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን ወንጀለኛ ከተባሉ የ10 ዓመት እስር እንደሚጠብቃቸው ፍራንስ 24 ዘግቧል።
ሳርኮዚ በ2012 ምርጫ ከተሸነፉ ወዲህ የተለያዩ ክሶች ተመስርቶባቸው ፍርድ ቤት እየተመላለሱ መሆናቸውም ተገልጿል።
በዚሁም እስካሁን በሁለት ክሶች የጥፋተኝነት ውሳኔ እንደተላለፈባቸው ነው የተገለጸው።
አሁን ላይ በሳርኮዚ ላይ የተመሰረተው ክስ ለአስርት ዓመታት ምርመራ ሲካሄድበት የነበረ ሲሆን በፈረንጆቹ 2007 ለተካሄደው የፈረንሳይ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ቅስቀሳ ከሊቢያው መሪ ህገ-ወጥ ገንዘቡን በመቀበል ወንጀል ነው ክስ የተመሰረተባቸው።
የፈረንሳይ ህግ የሌላ ሀገር ዜጎች ለፕሬዚዳንታዊ ዕጩዎች የምርጫ ቅስቀሳ የሚውል የገንዘብ ድጋፍ ማድረግን እንደሚከለክል ዘገባው አመላክቷል።