”ዳግማዊት ኢየሩሳሌም”
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት (ገና) በዓል በልዩ ሁኔታ በሚከበርባት ላሊበላ ከተማ በሦስት ምድብ የታነጹ የተለያዩ ቤተ-መቅደሶች ይገኛሉ፡፡
በየዓመቱ ታሕሣሥ 29 (በአራት ዓመት አንዴ በዘመነ ዮሐንስ ታሕሣሥ 28) የልደት (ገና) በዓል በላሊበላ ከተማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ተከታዮች እንዲሁም ጎብኚዎች በተገኙበት ይከበራል፡፡
የገና በዓል በላሊበላ በልዩ ሁኔታ የሚከበረው አንድም፥ ከአንድ አለት የተፈለፈሉት ቤተ-መቅደሶች የኢየሩሳሌም ምሳሌ (ዳግማዊት ኢየሩሳሌም) ተብለው በሐይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ ስለሚታመን ነው፡፡
በዚህም ወደ ኢየሩሳሌም ለመሔድ ሁኔታዎች ያልፈቀዱላቸው አማኞች እንዲሁም ጎብኚዎች ወደ ዳግማዊት ኢየሩሳሌም (ላሊበላ) በማቅናት መንፈሳዊ ሥርዓታቸውን ይፈፅማሉ፡፡
ሌላው ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ እና ቤተ-መቅደሶቹን ያነጸው ቅዱስ ላሊበላ የተወለዱበት ዕለት ተመሳሳይ መሆኑ ነው፡፡
በቅዱስ ላሊበላ ደብር አገልጋይ፣ ጸሐፊ እና አስጎብኚ ቀሲስ ፈንታ ታደሰ ከፋና ዲጂታል ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ ቅዱስ ላሊበላ በከተማዋ ውስጥ የሚገኙትን ቤተ-መቅደሶች ለማነጽ 23 ዓመታት እንደፈጀበት ተናግረዋል፡፡
ኪነ-ሕንጻውም በምድራዊት ኢየሩሳሌም፣ በሰማያዊት ኢየሩሳሌም እና በኖኅ መርከብ ምሳሌ ተደርጎ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
በአስተናነጽ ቅደም ተከተላቸው መሰረትም በምድብ አንድ በምድራዊት ኢየሩሳሌም የሚመሰሉት፥ ቤተ-ማርያም፣ ቤተ-መድኃኒዓለም፣ ቤተ-ጎልጎታ (ቤተ-ሚካኤል)፣ ቤተ-መስቀል እና ቤተ-ደናግል ናቸው ይላሉ፡፡
አቀማመጣቸው መስቀለኛ መሆኑን እና ልክ ክርስቶስ ሲሰቀል የተቸነከሩት ችንካር (ሳዶር፣ አላዶር፣ ዳናስ፣ አዴራ ሮዳስ) እንደሚባሉ በእነዚህ አቀማመጥ ልክ እንደሚገኝ ነው የሚገልጹት፡፡
በምድብ ሁለት የሚገኙት እና በሰማያዊት ኢየሩሳሌም የሚመሰሉት ደግሞ፥ ቤተ-ገብርዔል፣ ቤተ-አማኑኤል፣ ቤተ-መርቆርዮስ፣ ቤተ-አባ ሊባኖስ መሆናቸውን እና አራቱም በአንድ አቅጣጫ እንደሚገኙ አመላክተዋል፡፡
እንዲሁም በምድብ ሦስት ለብቻው የሚገኘው እና በኖኅ መርከብ ምሳሌ ተደርጎ የታነጸው የቅዱስ ላሊበላ የመጨረሻ ሥራ ቤተ-ጊዮርጊስ ነው ይላሉ፡፡
ቤተ-ጊዮርጊስ የአራቱ አቅጣጫዎች አመላካች ኖሮት በመስቀለኛ ቅርጽ የታነጸ ቤተ-መቅደስ ነው፡፡
ቅዱስ ላሊበላ ታሕሣሥ 29 ቀን 1101 ዓ.ም ተወልዶ፥ ከ1157 እስከ 1197 ለ40 ዓመታት በንግሥና ቆይቷል፡፡
በ1157 ዓ.ም ከቅዱስ ገብረ-ማርያም ንግሥናውን ከተቀበለ በኋላ፥ ከ1166 እስከ 1189 ለ23 ዓመታት አሥሩን ቤተ-መቅደሶች አንጿል፡፡
ኢትዮጵያውያን ቅዱስ ላሊበላ ያነጻቸውን ድንቅ ቤተ-መቅደሶች ጨምሮ ከላሊበላ ከተማና ላስታ ወረዳ የሚገኙትን ይምርሐነ ክርስቶስ፣ ነአኩቶሎአብ እንዲሁም አሸተን (አሽተን) ማርያምን በመጎብኘት የኢትዮጵያን ታሪክና ጥበብ ተረድተው ለሌሎች እንዲያሳውቁ ቀሲስ ፈንታ ታደሰ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው