ሐይማኖታዊ ሥርዓቶች በቅዱስ ላሊበላ ቤተ-መቅደሶች
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ካሳለፍነው ቅዳሜ ጀምሮ እስከ ታሕሣሥ 29 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ የሚቆዩ ከገና በዓል ጋር የተያያዙ ሐይማኖታዊ ሥርዓቶች በሦስት ቤተ-ክርስቲያኖች በልዩ ሁኔታ እየተከናወኑ ነው፡፡
በቤተ-መድኃኔዓለም፣ በቤተ-አማኑኤል እና በቤተ-ማርያም ሐይማኖታዊ ሥርዓቶቹ በልዩ ሁኔታ እየተከወኑ መሆኑን በቅዱስ ላሊበላ ደብር የቤተ-ክርስቲያን አገልጋይ እና አስጎብኚ ቀሲስ ፈንታ ታደሰ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል ሁሉም ቤተ-ክርስቲያኖች ሥጋ ወደሙ ለማቀበል ሥርዓተ-ቅዳሴ እንደሚፈጸምባቸውም አስገንዝበዋል፡፡
“በገና በዓል በሚቀርቡት ሐይማኖታዊ ሥርዓቶች ሁሉ ተመስጋኙም አምልኮቱም እግዚአብሔር ነው” ያሉት ቀሲስ ፈንታ፥ ገና (ልደት) በላሊበላ ልዩ የሚያደርገው የኢየሱስ ክርስቶስ እና የቅዱስ ላሊበላ ልደት አንድ ቀን መሆኑ ነው ይላሉ፤ የተወለዱበት ዓመተ ምኅረት መለያየት እንደተጠበቀ ሆኖ፡፡
በሐይማኖቱ ሥነ-ሥርዓት መሠረት በዚሁ የልደት በዓል አከባበር ላይ ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ፣ ቅዱስ ገብረ ማርያም፣ ቅዱስ ላሊበላ እና ቅዱስ ነአኩቶሎአብም ይመሰገናሉ ብለዋል፡፡
የቅዱስ ላሊበላ የመጀመሪያ ሥራ በሆነችው በቤተ-ማርያም ዙሪያ ዛሬ ለነገ አጥቢያ “ቤዛ ኩሉ ዓለም ዮም ተወልደ መድኃኔዓለም (የዓለም መድኃኒት፣ የዓለም ሁሉ ቤዛ ዛሬ ተወለደ)” እየተባለ ምሥጋና ይቀርባል ብለዋል፡፡
ይህም በላሊበላ ከተማ የሚከበረውን የገና በዓል ልዩ እንደሚያደርገው ነው ያስረዱት፡፡
“ልክ ከሰማይ መላዕክት እንደሚመጡ በቤተ-ማርያም ዙሪያ ባለው ማሜ ጋራ ካኅናቱ ካባና ሸማ በመልበስ እያሸበሸቡ እየሰገዱ ወደታችና ወደላይ ሲቃኑ በመላዕክት ምሳሌ ሥርዓቱን ያቀርባሉ” ሲሉም አስረድተዋል፡፡
እንዲሁም “ከታች ያሉት ካኅናት ሰባሠገልን ተመስለው አምሐ ይዘው ኮከብ እየመራቸው ወደ ቤተልሔሙ እንደሔዱ በመምሰል” ሥነ-ሥርዓት ይከናወናል ነው ያሉት፡፡
በዮሐንስ ደርበው