ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ ለገና በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል (ገና) የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ!
የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አምላክ ሰው የሆነበት በዓል መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ይነግሩናል፡፡
ይሄም የሆነበት ዓላማ የሰውን ልጅ ጉስቁልና በማስቀረት በዕርቅ አዲስ ሕይወትን ለመስጠት ነው፡፡ የሰው ልጅ በራሱ ዐቅም ይሄንን ማድረግ አልቻለም፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር አደረገለት፡፡ ሰው መሄድ የነበረበትን መንገድ እግዚአብሔር መጣ፡፡
ከዚህ የምንማረው ብዙ ነገር ነው፡፡ መልካም ነገር ለማድረግ የሌላን ወገን መጠበቅ የለብንም፡፡ እኛ መልካም መሆኑን እስካመንን ድረስ ዋጋ ከፍለንም ቢሆን፣ ራሳችንን ዝቅ አድርገንም ቢሆን፣ ብዙ ነገር ትተንም ቢሆን መልካሙን ነገር ማድረግ አለብን፡፡ ብዙዎች ወደ ሰላም መንገድ ለመምጣት ሌሎች ምን ይሉናል እንዲህና እንዲያ ቢያጋጥመኝስ ብቻዬን እንዴት እንደዚህ አደርጋለሁ ይላሉ፡፡
የጥበብ ሰዎች ያመኑበትን ነገር ፈጸሙ እንጂ የሀገራቸው ሰዎች ሁሉ እስኪያምኑ አልጠበቁም፡፡ እረኞች ያመኑበትን ነገር ፈጸሙ እንጂ የቤተልሔም ሰዎች ሁሉ እስኪያምኑ አልጠበቁም፡፡ የበረቱ እንስሳት እንኳን ትንፋሻቸው ለመገበር የሁሉንም እንስሳት ስምምነት አልጠበቁም፡፡
ዕርቅ የአዲስ ሕይወት መነሻ ነው፡፡ ሰው በሠራው ጥፋት ከራሱ ጋር፣ ከፈጣሪ ጋር፣ ከመላእክት ጋር፣ ከሰማያት ጋር፣ ከተፈጥሮ ጋር ተጣልቶ ነበር፡፡ ይሄም ነው የሰውን ልጅ ሕይወት የጉስቁልና ሕይወት አድርጎት የኖረው፡፡ እግዚአብሔር ወደ ቤተልሔም በረት ሲመጣ ግን መላእክትም መጡ፤ ሰማያትም ተከፈቱ፤ እንስሳትም ያላቸውን አበረከቱ፡፡ ይሄም ዘላቂ ዕርቅን አወረደ፡፡
ኢትዮጵያችን የጀመረችው የብልጽግና ጉዞ እንዲሳካ ዘላቂ ዕርቅ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ነው ከለውጡ መጀመሪያ አንሥቶ ስለ ዕርቅ በተደጋጋሚ የሚነገረው፡፡ እርስ በርሳችን መታረቅ፣ ከባህላችንና ከማንነታችን ጋር መታረቅ፣ ከፈጣሪያችን ጋር መታረቅ፣ ከሥልጣኔ ጋር መታረቅ ያስፈልገናል፡፡ በከብቶች በረት ከዚያ በፊት ተገናኝተው የማያውቁ አካላት ተገናኝተዋል፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ፣ መላእክት፣ እረኞች፣ የጥበብ ሰዎች፡፡ ስለ ቀድሞው አልተነጋገሩም፡፡ እርሱ አልፏልና፡፡ ስለቀጣዩ አዲስ ሕይወት ግን ሁሉም ተናግረዋል፡፡ ሁሉም የሚገባቸውን አድርገዋል፡፡
እኛም የሚያስፈልገን ይሄ ነው፡፡ ነባር ጓዛችንን እንተውና በሀገራዊ ምክክሩ ላይ ለአዲሱ ሀገራዊ ሕይወት ስንል እንገናኝ፡፡ ከዚህ በፊት በጥላቻ ብንተያይም እርሱን በቃ እንበል፡፡ ሰውና መላእክት ተጣልተው ነበር፡፡ ቤተልሔም አገናኘቻቸው፡፡ ሕዝብና አሕዛብ ተጣልተው ነበር፡፡ ቤተልሔም አገናኘቻቸው፡፡ ሰውና አምላክ ተጣልተው ነበር፡፡ ቤተልሔም አገናኘቻቸው፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ የተለያየን ሁሉ ብሔራዊ ምክክሩ እንደ ቤተልሔም ሊያገናኘን ይገባል፡፡ እስከ ቤተልሔም ያለውን ትተን፣ ከቤተልሔም ወዲያ ያለው አስበን እንምጣ፡፡
ኑ ወደ ምክክር ጉባኤው፤ ኑ ወደ ሰላሙ መንገድ፡፡ ያለፈውን ነገር እንተወዉ፡፡ አንቀይረውምና፡፡ መጀመሪያ ከራሳችን ጋር እንታረቅ፡፡ ከራሱ ጋር የታረቀ ሁሉ ከሌሎች ጋር መታረቅ ከባድ አይሆንበትም፡፡ እረኞች በረታቸውን ለመልቀቅ አልከበዳቸውም፡፡ የጥበብ ሰዎች ከሩቅ ሀገር ለመምጣት አልከበዳቸውም፡፡
መላእክት ወደ አንዲት መንደር ለመውረድ አልከበዳቸውም፡፡ ከራሱ ጋር የታረቀ ሁሉ ለሰላም ሲባል ማናቸውን መሥዋዕትነት ለመክፈከል አይከብደውም፡፡ ክብር፣ ሥልጣን፣ ፕሮቶኮል እና የመሳሰሉት ሁሉ ከራሱ ጋር ለታረቀ ሰው ዕንቅፋቶች አይደሉም፡፡
ከራሱ ጋር የታረቀ ሰው ትናንትን ሳይሆን ነገን ያያል፡፡ ሰዎች ቢቃወሙት እና ባይገባቸውም እንኳን፣ እውነት የሆነውን ነገር ለማድረግ ጉልበት ይኖረዋል፡፡ ታሪክን ይቀይራል፡፡ ታሪክ ሲቀየርም ያያል፡፡ የቤተልሔም ሰዎች ከራሳቸው ጋር ስላልታረቁ ድንግል ማርያምን እና ኢየሱስ ክርስቶስን በቤታቸው ለማስተናገድ ፈቃደኞች አልነበሩም፡፡ ታሪክ ለመቀየርም፣ ታሪክ ሲቀየር ለማየትም ፈቃደኞች አልነበሩም፡፡ በዚህ የተነሣ የልደት በዓል በተከበረ ቁጥር ሲወቀሱ ይኖራሉ፡፡
እኛም በኢትዮጵያ የነገ ታሪክ ውስጥ እንደ ቤተልሔም ሰዎች ከሚወቀሱት መካከል እንዳንሆን መጀመሪያ ከራሳችን ጋ እንታረቅ፤ ከዚያም ከነገ ጋር ለመታረቅ ዕድል እናገኛለን፡፡ ከነገ ጋር የታረቀ ሰው ከየትኛውም ወገን፣ ከማንኛውም ሐሳብ ጋር ዕርቅን ከመፍጠር ወደ ኋላ አይልም፡፡
በዚህ የልደት በዓል ሁላችን ከራሳችን ጋር ታርቀን ከነገዋ ኢትዮጵያ ጋር እንድንታረቅ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
በድጋሚ መልካም የልደት በዓል ይሁንልን፡፡