የተረጋገጠው ሰላም ለተሰሩት የልማት አውታሮች ጉልህ ሚና አለው – አቶ ሙስጠፌ መሀመድ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሶማሌ ክልል የተረጋገጠው አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት ለተሰሩት የልማት አውታሮች ጉልህ ሚና እንዳለው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ ገለፁ።
ብልፅግና ፓርቲ “ከቃል እስከ ባህል” በሚል መሪ ቃል ባለፉት አምስት አመታት በሁሉም ዘርፎች የተገኙትን ድሎች ለማስቀጠል ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ዛሬ ውይይት ማካሄድ ጀምሯል።
አቶ መስጠፌ በዚህ ወቅት÷ በክልሉ ከአንደኛው የብልፅግና ፓርቲ ጉባኤ ማግስት ቃል ከተገቡት አንኳር የልማት ስራዎች መካከል ግብርናና የሌማት ትሩፋት አንዱ እንደነበረ ገልፀዋል፡፡
በዚህም በሶማሌ ክልል ከለውጡ በፊት ይታረስ የነበረው 350 ሺህ ሄክታር መሬትን በ3 እጥፍ በማሳደግ ወደ 1 ነጥብ 1 ሚሊየን ሄክታር ከፍ ማድረግ ተችሏል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በሶማሊ ክልል የተረጋገጠው አስተማማኝ ሰላምና የፖለቲካ መረጋጋት ለተሰሩት ዘርፈ ብዙ የልማት አውታሮች ጉልህ ሚና እንዳለው አንስተዋል፡፡