የከተማ አስተዳደሩ ከባለሃብቶች ጋር በመተባበር የገነባቸው ቤቶች ለነዋሪዎች ተላለፉ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከከተማው ባለሃብቶች ጋር በመተባበር የገነባቸውን ቤቶችና የመስሪያ ቦታዎች ለነዋሪዎች አስተላለፈ፡፡
የአስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ÷ በለሚ ኩራ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ እና በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች ከባለሃብቶች ጋር በመተባበር የተገነቡ ቤቶች እና የስራ እድል ለተፈጠረላቸው የልማት ተነሺ የከተማው ነዋሪዎች የመስሪያ ቦታዎች መተላለፋቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡
በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ብቻ በኮሪደር ልማትና በመንገድ ወሰን ማስከበር ለተነሱ 4 ሺህ 510 እማወራ እና አባወራዎች ንጹህ እና መሠረተ ልማት የተሟሉላቸው መኖሪያ ቤቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ገንብተን አስተላልፈናል ብለዋል።
በተጨማሪም ከ1 ሺህ 264 በላይ ለሚሆኑ ነዋሪዎች የሥራ እድል ፈጥረን የመስሪያ ቦታዎችን አስረክበናል ሲሉ ገልጸዋል።
በዚህም አራት ህንጻዎች በአያት ሪል ስቴት፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ጄ ኤፍ ኤም ፔትሮሊየም ዲስትሪቢዩሽን እና በለሚኩራ ክፍለ ከተማ የተገነቡ ሲሆን በተጨማሪም በላይነህ ክንዴ ግሩፕ በአቃቂ ቃሊቲ 48 ቤቶችን እንዲሁም በንፋስ ስልክ ላፍቶ 141 ቤቶች ተገንብተው መተላለፋቸውን ገልጸዋል::
መንግስት ያቀረበውን ጥሪ በመቀበል ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን የተወጡ ባለሃብቶችም ከንቲባ አዳነች አቤቤ ምስጋና አቅርበዋል፡፡