Fana: At a Speed of Life!

የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ለሰው ልጆች ፍቅርን በመስጠትና በመረዳዳት ማክበር ይገባል – የሃይማኖት አባቶች

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሕዝበ ክርስቲያኑ የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓልን ለሰው ልጆች ፍቅርንና ሰላምን በመስጠት እንዲሁም በመረዳዳትና በአብሮነት ማክበር እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች ገለፁ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን እና የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስትያናት ህብረት አባቶች የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል በማስመልከት ለመላው የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት እግዚአብሔር ሰውን የመውደዱ ዐቢይ ማሳያ ነው ብለዋል።

በዓለ ልደትን ስናከብር ነገረ እግዚአብሔርን፣ ነገረ ፍቅርን፣ ነገረ እርቅና ነገረ ሰላምን በማኅበረሰብ የማስረፅ ሃሳብ ይዘን ሊሆን ይገባልም ነው ያሉት።

የልደተ ክርስቶስ በዓል የእግዚአብሔር በዓል በመሆኑ፥ እግዚአብሔር በምድሪቱ ሰላም እንዲያወርድ በመጸለይ፣ እርስ በርስ በመዋደድ፣ በፍቅር እና በእርቅ ማክበር እንደሚገባ አባታዊ ጥሪ አቅርበዋል።

በተጨማሪም ህብረተሰቡ አቅመ ደካሞችን በመደገፍ በዓሉን በአብሮነት እንዲያከብርም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል በበኩላቸው÷ በዓለም ዙሪያ ላሉ የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ሁሉ እንኳን ለብርሃነ ልደቱ በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል፡፡

የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን ስናከብር ጎረቤቶቻችንን በመጠየቅ፣ የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት፣ የታመሙትን በመጠየቅ ሊሆን ይገባል ነው ያሉት፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ወደዚህች ምድር ሲያመጣው በሰላምና በደስታ እንዲኖር ነው ያሉት ብጹዕ ካርዲናሉ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት ጊዜ ሰላም በምድር የሚል ድምጽ መሰማቱ የሰላም አስፈላጊነትን ይበልጥ እንዲጎላ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ለሰላም መጠበቅ ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንዳለበት ጠቅሰው፥ በራስ ላይ እንዲደረግ የማይፈቅደውን በሌሎች ላይ ባለማድረግ ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ መስራት እንዳለበትም አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስትያናት ህብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ፃዲቁ አብዶ፥ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የሰላም፣ የጤና እና የብልጽግና እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል።

ህዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን ሲያከብር ለሰው ልጆች የከፈለውን ውድ ዋጋ በማስታወስ በአክብሮትና በፍቅር ማክበር እንደሚገባ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለመገንባት የሚደረጉ ጥረቶችን በማገዝ ገንቢ ሚና መጫወት አለብን ነው ያሉት።

በዓሉን አቅመ ደካሞችና የተቸገሩትን በመርዳት፣ በመጠያየቅ፣ በአንድነትና በአብሮነት ማክበር እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.