Fana: At a Speed of Life!

የሀገር ባለውለታ …

 

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በምዕራብ ወለጋ ዞን ቦጂ ድርመጂ ወረዳ ከአቶ ደመቅሳ ሰንበቶ እና ወ/ሮ ናንሲሴ ሰርዳ ተወለዱ፡፡

የቤተሰቡ አራተኛ እና ብቸኛ ወንድ ልጅ የሆኑት አቶ ቡልቻ አባታቸውን ገና በለጋ እድሜያቸው ነበር ያጡት፡፡

አጎታቸውም የአባታቸውን አደራ ተቀብለው እንደ አባት በመሆን አሳድገዋቸዋል፡፡

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በጊንቢ እንዲሁም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በኩየራ አድቬንቲስት ትምህርት ቤት ተምረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኢኮኖሚክስ የትምህርት መስክ በመከታተል ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ተመርቀዋል፡፡

ከፍተኛው ውጤት በማምጣታቸውም አሜሪካ ኮርኔል ዩኒቨርሲቲ የትምህርት እድል አግኝተው ወደ ስፍራው ከተጓዙ በኋላ ብዙ ኢትዮጵውያን ተማሪዎች ወደሚገኙበት ሲራኪዩዝ ዩኒቨርሲቲ ተዘዋውረው በኢኮኖሚክስ ዘርፍ ትምህርታቸውን ተከታትለው ሁለተኛ ዲግሪ ተቀብለው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡

በትምህርት ቆይታቸው ባሳዩት ብቃትም በዩኒቨርሲቲው ልዩ ተሸላሚ ነበሩ፡፡

የስራ ህይወታቸውን ተማሪ ሳሉ በመምህርነት የጀመሩ ሲሆን በውጭ ሀገር ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ሳሉም በገንዘብ ሚኒስቴር ጥሪ ተደርጎላቸው በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ውስጥ በበጀት ዳይሬክተር፣ ረዳት ሚኒስትር እንዲሁም ምክትል ሚኒስትር በመሆን ለሰባት ዓመታት አገልግለዋል፡፡

በመቀጠል በተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (ዩኔንዲፒ) እና በዓለም ባንክ 20 የአፍሪካ ሀገራትን በመወከል ሰርተዋል፡፡

አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከምጣኔ ሃብት አበርክቶአቸው ባሻገር በሀገሪቱ ዴሞክራሲ እንዲስፋፋ የፖለቲካ ዓለምን በመቀላቀል የራሳቸውን አሻራ አሳርፈዋል፡፡

በአቋማቸው ጽኑ፣ ሕዝቦችን ለማቀራረብ የተጉ፣ እውነት ነው ብለው ያመኑበትን የሚናገሩ ሰው እንደነበሩም ይነገራል፡፡

በልጅነታቸው ትዳር የመሰረቱት አቶ ቡልቻ የስድስት ልጆች አባት ነበሩ፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.