ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) ለገና በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የገና በዓልን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረሳችሁ
ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚነግሩን ሕግ ጥሶ ከእግዚአብሔር ጋር የታጣላው ራሱ የሰው ልጅ ነበረ፡፡ ዕርቅን አውርዶ ሰላምን ለማስፈን በረት ድረስ የመጣው ግን እግዚአብሔር ነው፡፡ እንደ ቅዱሳት መጻሕፍት አስተምህሮ እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ፣ አሸናፊ፣ የሚሳነው አንዳች የሌለ ነው፡፡ ነገር ግን ለዕርቅ እና ለሰላም ሲል ወደ ማይገባው ሥፍራ መጣ፡፡ አሸናፊ ቢሆንም እንደ ተሸናፊ ሆነ፡፡ ዐቅም ቢኖረው እንደ ዐቅመ ቢስ ሆኖ ታየ፡፡ በሁሉ ሀብታም ሲሆን፣ ራሱን ታናሽ አደረገ፡፡ ይህ ሁሉ ለዕርቅና ለሰላም የተከፈለ የታላቅነት ዋጋ ነው፡፡
እግዚአብሔር ለዕርቅ እና ለሰላም ሲል በደካማዋ ከተማ በቤተልሔም፣ በተናቀችው ሥፍራ በበረት መገኘቱ የገባቸውም ያልገባቸውም ነበሩ፡፡ የገባቸው፤ ከሰማየ ሰማያት ወርደው “ሰላም እና ዕርቅ በምድር ይሁን” ብለው ዘመሩ፡፡ የገባቸው፤ ከምሥራቅ ኮከቡን አይተው፣ እጅ መንሻውን ይዘው መጡ፡፡ የገባቸው፤ በረታቸውን ለቅቀው ለድንግል ማርያም እና ለኢየሱስ ክርስቶስ ሰጡ፡፡ የገባቸው፤ የሰማይ መላእክቱን ተከትለው ወደ በረት ሄደው እርቅና ሰላምን አመሰገኑ፡፡
ያልገባቸው ሰዎች፣ የዕርቅ እና የሰላሙ ዐዋጅ እየታወጀ እነርሱ ግን ተኝተው ነበር፡፡ የመንደር ጌቶች እነ ሄሮድስ፣ የሰው ልጅ ሰላም ማግኘት ሳይሆን ከጠላት ያገኙት ሥልጣን ያስጨንቃቸው ነበር፡፡ የይሁዳ ሰዎች፤ ዓለም በማይመለስበት ሁኔታ እየተቀየረ፣ እነርሱ ግን እየሆነ ያለውን ለውጥ አያዩም አይሰሙም ነበር፡፡ ከሰማይ መላእክት ወርደው፣ ከምድር እረኞች ነቅተው ተአምር ሲሠራ፤ እነርሱ ግን በዕንቅልፍ ደንዝዘው ነበር፡፡እ ነርሱ እያንቀላፉ ከተማቸው ቤተልሔም ተቀይራለች፡፡ የእንጀራ ቤት ሆናለች፡፡ ታሪኳ ተቀይሯል፡፡ ታናሽ ከተማነቷ ተቀይሯል፡፡
ያልገባቸው፣ ሰላምና ዕርቅ ሲባሉ የድካምና የዐቅመ ቢስነት ምልክት አድርገው ተመለከቱት፡፡ ሰይፍና ጎራዴ የለመዱ፤ መግደልና ማጥፋት ጀግንነት የሚመስላቸው ነበሩና፡፡ ሰላም ድካም፣ ዕርቅም ሽንፈት ይመስላቸው ነበር፡፡ ስለዚህም በእኩለ ሌሊት ከመሸ፣ በከብቶች በረት ለሁሉ የመጣውን ሰላም አቅለው አንቀበልም አሉ፡፡ እነ ሄሮድስ ሰይፍ መዘዙ፡፡ ሰላምን አሳደዱ፤ ሰላማዊ ሕጻናትንም ፈጁ፡፡ ሄሮድስ የገዛ ሕዝቡን ለመጨፍጨፍና ለመግዛት በጠላት የተሾመ ሰው ነበር፡፡ የሚያስፈጽመው የእሥራኤል ጠላቶችን ዓላማ ነበረ፡፡
ይሄንን በዓል የምናከብር፤ ወይ ሰላምና ዕርቅን ከሚወዱት ወገን ነን፡፡ አለያም ሰላምንና ዕርቅን ከሚያሳድዱት ወገን ነን፡፡ መንግሥት ሰላምና ዕርቅን ደጋግሞ የሚያውጀው ዐቅም ከማጣት፣ ጉልበቱ ከመድከም የተነሣ አይደለም፡፡ ሁሉም ዓይነት መንግሥታዊ ዐቅሞች በእጁና በደጁ አሉ፡፡ ሰላምና ዕርቅ ግን ከሁሉ በበለጠ፤ ዘመን አሻጋሪ፣ ታሪክ ቀያሪ፣ የችግርና መከራ ዘመን ማብቂያ መፍትሔዎች በመሆናቸው ነው፡፡ ሁሉን አሸናፊ፣ ሁሉን አሻጋሪ ያደርጋሉ፡፡ ጠባሳ ሳይተዉ ቁስልን ያሽራሉ፤ ለልጅ ልጅ ቂምን ሳይሆን ሐሴትን ያወርሳሉ፤ ከመጠፋፋት ይታደጋሉ፡፡ የሰላምና የዕርቅ መንገድ የሚመረጠውም ለዚህ ነው፡፡
ሰላምና ዕርቅን መምረጥ፤ የኃያል ባለ-ራዕይ፣ የፍጹማዊ-አሸናፊና ባለታላቅ-ዐቅም በውዴታ የሚሸከመው የከፍታ ግዳጅ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሁሉን ማድረግ ይችል ነበር፡፡ ሰላምን እያወጀ ወደ ከብቶች በረት የመጣው ግን እርሱ ኃያሉ ነው፡፡ የአዳም ልጆች በሠገነት ሲወለዱ የእግዚአብሔር ልጅ ነው በበረት የተወለደው፡፡ እግዚአብሔር ነው ለሰላምና ለዕርቅ ሲባል ከቤተልሔም እስከ ቀራንዮ መከራን የተቀበለው፡፡
መንግሥት ዛሬም ለሰላም እና ለዕርቅ እጁ እንደተዘረጋ ነው፡፡ ለሁሉ የሚሆን ሰላም በኃይል ሳይሆን በፍቅር መንገድ እንደሚመጣ ያውቃል፡፡ ለሰላምና ለዕርቅ በመሸነፍ ውስጥ ፍጹማዊ ማሸነፍ እንዳለ ያምናል፡፡ ጥቂቶች እንጂ ብዙኃኑ ከሰላም የሚገኘውን ክፍያ የሚሹ እንደሆነ ይረዳል፡፡
የጠላት መሣሪያ የነበረውን የሄሮድስን መጨረሻ ማየት ነው፡፡ ለሰላምና ለዕርቅ ጀርባቸውን የሰጡ የቤተልሔም ከተማ ሰዎችን ፍጻሜ ማሰብ ነው፡፡ እግዚአብሔር በረት ድረስ ሲፈልጋቸው አሻፈረኝ ብለው ነበር፡፡ ከዓመታት በኋላ በኃይልና በጉልበት ሲጎበኛቸው ግን፣ ፈልገው ሊያገኙት አልቻሉም፡፡ ቤታቸው የተፈታ ሆኖ ቀረ፡፡ ከዚያ በኋላ ፍለጋቸው መባከንና መቅበዝበዝ ሆነ ፡፡ ዕርቅና ሰላምን የሚገፋ ሁሉ መጨረሻው እንደዚህ ነው፡፡
ሁሉም ጊዜ አለው፡፡ በጊዜው መጠቀም የጠቢባን ድርሻ ነው፡፡ ለሰላም የተዘረጉ እጆች እንደተዘረጉ አይቀሩም፡፡ ለሰላም ሲባል ወደ ምድር የወረዱ ሁሉ እንደ ወረዱ አይቀሩም፡፡ ለሰላም ሲባል ደካሞች መስለው የታዩ ሁሉ፣ ኃይላቸው በጊዜው ይገልጣሉ፡፡ የግድግዳው ጽሑፍ ይመጣል፡፡ የተዘረጋው ብራና ይጠቀለላል፡፡
ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ሦስቱ ሰላማውያን ቦታ አላገኙም ነበር፡፡ የጥበብ ሰዎች፣ እረኞች እና መላእክት፡፡ ሦስቱም ብዙዎቹ ያደረጉትን ለማድረግ የመጡ አልነበሩም፡፡ ትክለኛውን ነገር ለማድረግ እንጂ፡፡ ሦስቱም ዘመን የወለደውን ጊዜ የወደደውን አልተከተሉም፡፡ የሚጠቅመውን ነገር እንጂ፡፡ ታሪክ እንደሚያስተምረን ግን የእነዚህ የሦስቱ እውነት በጊዜው ተገልጧል፡፡ ዓለምም በየዓመቱ የክርስቶስን ልደት ሲያከብር እነዚህን ሦስቱን ሰላማውያን ያስታውሳል፡፡
ለሰላም ስትሉ ዋጋ የምትከፍሉ፣ የምትዋረዱና የምትቃለሉ ሁሉ ከሦስቱ ሰላማውያን መማር አለባችሁ፡፡ የጠላት መሣሪያዎች የሆኑት ሄሮድሳውያን ቢገድሉም፤ የቤተልሔም ሰዎች እምቢ ቢሉም፣ የተማሩ የተባሉት የአይሁድ ሊቃውንት ቢቀልዱም፣ ለሰላም ዋጋ መክፈል ያዋጣል፡፡ ቢያንስ ሰማያዊና ታሪካዊ ዋጋ ያስገኛል፡፡
ይሄንን በዓል ስናከብር ከሦስቱ ሰላማውያን ጋር ሆነን ሰላምና ዕርቅ በሀገራችን እንዲሰፍን የበኩላችንን በማድረግ እንዲሆን ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡ እርስ በርስ ከመሸናነፍ ስለሰላም ሁላችንም ብንሸነፍ ሁላችንንም አሸናፊ ያደርገናል፡፡ መንግሥት ለሰላማዊ መንገዶች ቅድሚያ ይሰጣል፡፡ ለሰላም ከሚሠሩት ጋር ሁሉ አብሮ ይሠራል፡፡ ሰላማውያን ለሚከፍሉት መሥዋዕትነት ክብርና ዋጋ ይሰጣል፡፡
በድጋሜ መልካም በዓል ይሁን፡፡
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ታህሳስ 28፣ 2017 ዓ.ም