Fana: At a Speed of Life!

ከ2 ሚሊየን በላይ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ተባለ

 

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ስድስት ወራት ከ2 ሚሊየን በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ባለፉት ስድስት ወራት ከክህሎት ልማት፣ ሥራ ዕድል ፈጠራ እና ከአሰሪና ሠራተኛ ግንኙነት አኳያ አበረታች ተግባር ተከናውኗል ብለዋል።

በሀገር ውስጥ፣ በውጭ ሀገርና በሌሎች አማራጮች ዜጎችን በቋሚነት የስራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸው፤ ባለፉት ስድስት ወራት የተሰራው ሥራ አበረታች ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ከ2 ሚሊየን በላይ ለሆኑ ዜጎች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ጠቅሰው፤ 1 ነጥብ 7 ሚሊየን በሀገር ውስጥ እንዲሁም 300 ሺህ በውጭ ሀገር ቋሚ የሥራ ዕድል እንደተፈጠረ ጠቁመዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ የተደረገው የ5 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ ስልጠና ኢኒሼቲቭ የዲጂታል ክህሎት በማሳደግ ለስራ ዕድል ፈጠራ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የስራ ዕድል ፈጠራው በቀጣይ ወራት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጽ ሚኒስቴሩ በ2017 በጀት አመት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ4 ነጥብ 9 ሚሊየን ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር አቅዶ እየሰራ ይገኛል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.