Fana: At a Speed of Life!

አየር ኃይሉን ቀዳሚ ተቋም ለማድረግ የተያዘው ራዕይ በትክክለኛው መስመር እየተጓዘ ነው – ሌ/ጄ ይልማ መርዳሳ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አየር ኃይል በ2022 ከአፍሪካ ቀዳሚ ተመራጭ የአቪዬሽን ተቋም ለማድረግ የተያዘው ራዕይ በትክክለኛው መስመር እየተጓዘ መሆኑን የአየር ሃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ፡፡

ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ አየር ኃይሉ እያከናወናቸው የሚገኙ እንቅስቃሴዎች ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አየር ኃይሉ በየዘመናቱ ሁሉ የተሰጡትን ሀገራዊ ግዳጅና ተልዕኮዎችን በአስተማማኝ ብቃት እየተወጣ ዛሬ ላይ የደረሰ በድልና በመስዋዕትነት የደመቀ አኩሪ ታሪክ ያለው አንጋፋና ስመ ገናና የአቪዬሽን ተቋም እንደሆነ አንስተዋል፡፡

አሁንም ዘመኑን በዋጀ መልኩ ተደራጅቶ የኢትዮጵያን የአየር ክልል በንቃት እየጠበቀ እንደሚገኝም ነው የገለጹት፡፡

ተቋሙ ዘመናዊ የስልጠና ሂደትን በመከተል ብቃት ያላቸው ተተኪ ባለሙያዎችን ለማፍራት ትኩረቱን የአየር ኃይል አካዳሚ ላይ በማድረግ የዘመኑን የአቪዬሽን ቴክኖሎጂ መጠቀም የሚችሉ በርካታ ባለሙያዎችን እያፈራ የሚገኝ መሆኑንም ገልፀዋል።

አመራሩ የተጀመሩ ሁሉን አቀፍ ሥራዎች አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበው፤ “ለታላቅ ሀገር ታላቅ አየር ኃይል” በሚል መርህ የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚመጥን ተቋም ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም በሰው ኃይል አቅም ግምባታ፣ በውጊያ መሰረተ ልማት ግምባታ፣ አዳዲስ ትጥቆችን በመታጠቅና በማሻሻል እንዲሁም ምቹና ፅዱ የስራ አካባቢን በመፍጠር ረገድ አመርቂ ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሉንም ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል በ2022 ከአፍሪካ ቀዳሚ ተመራጭ የአቪዬሽን ተቋም ለማድረግ የተያዝነው ራዕይ በትክክለኛው መስመር እየተጓዘ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል፥ በአሁኑ ወቅትም ሀገራችንን ከውጭም ሆነ ከውስጥ የጥፋት ቡድኖች ለመከላከል በሚያስችል ቁመና ላይ እንደሚገኝ መናገራቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.