Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ለገና በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ለገና በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ለገና በዓል ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለ2017 ዓ.ም ለጌታችን፣ ለአምላካችን እና ለመድሃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም እና በጤና አደረሠን፣ አደረሳችሁ!

በሀገር ውስጥ እና በመላዓው ዓለም በሙሉ የምትገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባለጠጋ የሆነው እግዚአብሔር ዘመናትን አሻግሮ ለ2017 ዓ.ም ለመድሃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል እንኳን በጤና አደረሰን፣ አደረሳችሁ በማለት በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ እና በራሴ ስም የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ለማስተላለፍ እወዳለሁ፡፡

ውድ የሀገራችን ሕዝቦች የጌታችን የመድሀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የድህነታችን ተስፋ እውን እንደሚሆን የተበሠረበት፣ ለሠው ልጆች የአዲስ ምዕራፍ ጅማሬ፣ በሀጢያት ምክንያት ከእግዚአብሔር ጋር ተጣልቶ እና ርቆ ለነበረው ሕዝብ ወደ እግዚአብሔር የመመለሡ ተስፋ የተረጋገጠበት ታላቅ የድል ብስራት ጅምር ነው፡፡

ብርሃነ ልደቱ ከእግዚአብሄር ርቀው ለነበሩ ሕዝቦች ወደ ራቁት ፈጣሪ የመመለሻ ደውል የተደወለበት፣ ወደ እግዚአብሔር የመቅረብ ተስፋ እርግጠኝነት የተበሠረበት፣ መለያየት በዕርቅ የሚተካበት ጊዜ እንደተቃረበ በተግባር የተረጋገጠበት ታላቅ ክብረ በዓል ነው፡፡

በሌላ በኩል ብርሃነ ልደቱ ለሰው ልጆች ጠላት ለሆነው ዳያቢሎስ ደግሞ የሃዘን፣ የሽንፈት፣የውርደት እና የውድቀት ምልክት ሲሆን ለእኛ ለምናምነው ግን ከጨላማ ወደ ብርሃን፣ ከኩነኔ ወደ ጽድቅ፣ ከሞት ወደ ሕይወት የመሸጋገር ጅምር የተበሰረበት የአዲስ ተስፋ፣ የበረከት፣ የመታደስ እና የክብር ድንቅ ማሳያ ነው፡፡

ጌታችንና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከብቶች በረት ውስጥ በመወለድ ትህትናን፣ ለእግዚአብሔር ፈቃድ መታዘዝን እና መገዛትን፣ ለሌሎች ጥቅም ሲባል ዝቅ ማለት እንደሚያስፈልግ ያስተማረበት ከፍያለ ክስተት ነው፡፡

ከብርሃነ ልደቱ ብዙ መልካም ትምህርቶችን መማር እንችላለን፡፡ በተለይም ከላይ እንደተገለጸው ትህትናን፣ ለሌሎች ጥቅም ሲባል መሰዋትነት እስከ መክፈል ድረስ መሰጠት እንደሚያስፈልግ፣አገልጋይነትን፣ ፍቅርን እና እርህራሄን ከትምህርቶቹ መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡

በመሆኑም ይህን ታላቅ የብርሃነ ልደቱን አስተምህሮ እና ምሳሌ በሕይወታችን በተግባር በመተርጎም ለሰው ልጆች ሁሉ ጥቅም በሚያመጡ አገልግሎቶች ላይ በንቃት እና በትጋት በመሳተፍ የጌታችን የመድሃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ፈለግ በተግባር መከተል ይጠበቅብናል፡፡

ይህን የከበረ በዓል በምናከብርበት ጊዜ ለሃገራችን ሰላም እና ለሕዝባችን አንድነት በመፀለይ፣ ራሳችንን ሰላማዊ በማድረግ እና ሌሎች ዜጎችም የተሟላ ሰላም ያገኙ ዘንድ ኃላፊነታችንን ከምንጊዜውም በላይ ለመወጣት በመወሰን እና በተግባርም በመተርጎምም መሆን አለበት፡፡

በተያያዘም ልደቱን ስናከብር የተቸገሩትን በመርዳት እና በመደገፍ፣ በሕመም አልጋ ላይ የሚገኙትን ወገኖቻችንን በመጠየቅ፣ በማበረታታት እና በመርዳት፤በሕግ ጥላስር በመሆን በተለያዩ ማረሚያ ቤቶች የሚገኙትን የሕግ ታራሚ ወገኖቻችንን በመጎብኝት እና በማበረታታት ሊሆን ይገባል፡፡

ጌታችንና መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲወለድ ሰብአ ሰገል ልዩ ገፀ በረከቶች ይዘው በቤተልሄም እንደተገኙ ሁሉ እኛም አማኞች በአንድ ልብና በአንድ መንፈስ በመሆን ባለን
ዕውቀት፣ ፀጋ እና ሃብት አብያተ ክርስቲያናትን ከዚያም ባለፈ ሀገራችንን ኢትዮጵያን ማገልገል እና መደገፍ ይጠበቅብናል፡፡

ለኔ ወይም ለእኛ ምን ተደረገልን ከሚል አስተሳሰብ ወጥተን እኔ ወይም እኛ ለሃገር እና ለሕዝብ ምን አደረግን የሚለውን በማሰብ እና እራሳችንን በመፈተሽ ከእኛ ለሃገራችን እና ለሕዝባችን ይገባል ብለን የምናስበውን መልካም ነገር ሁሉ ሳንቆጥብ ማበርከት ተገቢ ነው፡፡

በተለይም ሀገራችን ኢትዮጵያ የሠላም፣ የአንድነት፣ የፍቅር እና የእድገት ተምሳሌት ትሆን ዘንድ በተሰማራንበት የሥራ እና የአገልግሎት መስክ ሁሉ አቅም የፈቀደውን ሁሉ
እንድናበረክት በድጋሜ የአክብሮት ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡

በመጨረሻም እንኳን ለብርሃነ ልደቱ በድጋሚ አደረሰን አደረሳችሁ በማለት በአገልጋይነት መንፈስ ለሕዝብና ለሃገር ጥቅም በጋራ እንድንቆም እና እንድንሠራ የአደራ መልዕክቴን አቀርባለሁ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡

ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን ይባርክ ይጠብቅ!

ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ጸሐፊ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.