Fana: At a Speed of Life!

ሕብረተሰቡ በበዓል ሰሞን ሊከሰቱ ከሚችሉ አደጋዎች እራሱን እንዲጠብቅ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከመጪው የገና በዓል ጋር ተያይዞ ሕብረተሰቡ የኤሌክትሪክና ከሰል አጠቃቀምን ጨምሮ ድንገተኛ አደጋ ከሚያስከትሉ ሁኔታዎች እራሱን እንዲጠብቅ ጥሪ ቀረበ፡፡

የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በአደጋ ቅነሳ እና አደጋ ምላሽ ዘርፍ አተኩሮ ወደ ሥራ መግባቱን የተቋሙ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ንጋቱ ማሞ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡

የአደጋ ቅነሳ ዘርፉ ሕብረተሰቡ ለአደጋ የሚያጋልጡ አሠራሮችን ተረድቶ እራሱን ከአደጋ እንዲከላከል የሚያስችል መሆኑን አስረድተው÷ ይህን ለማስረጽም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በበዓላት ወቅት እሳትና የኤሌክትሪክ ኃይል ምንጮች በከፍተኛ ሁኔታ ለረጅም ጊዜ ጥቅም ላይ መዋላቸውን ተከትሎ አደጋዎች ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ ሕብረተሰቡ የኮሚሽኑን የጥንቃቄ መልዕክቶች በመተግበር በዓሉ ያለምንም አደጋ ተከብሮ እንዲያልፍ አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

ሁሉንም የበዓል ሥራዎች በተመሳሳይ ጊዜ ከመሥራት በመቆጠብ በቅደም ተከተል እንደቤተሰብ አባል ብዛትና ችሎታ ሥራ መከፋፈል እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

በአንድ ኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ላይ ደራርቦ አለመጠቀም፣ ሲሊንደር ከመለኮስ በፊት ያፈተለከ ጋዝ አለመኖሩን ማረጋገጥ እና በከሰል ጭስ መታፈን እንዳይከሰት በርና መስኮት በመክፈት በቂ የአየር ምልልስ እንዲኖር ማድረግ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።

እንዲሁም ሥራዎች ሲጠናቀቁ ምድጃውን ከቤት በማውጣት ቤቱን ማናፈስ፣ የተለኮሰ ሻማ ካለ አልባሳትን ጨምሮ ከተቀጣጣይ ነገሮች ማራቅ እና ከመተኛት በፊት ወይም ከቤት ሲወጡ ሻማውን ማጥፋት ያስፈልጋል ሲሉ ገልጸዋል።

ከዚህ አልፎ ለሚያጋጥሙ አደጋዎች የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች፣ ማሽነሪዎች እና አምቡላንሶች ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

አደጋዎች ካጋጠሙም ሕብረተሰቡ  በነፃ የስልክ መስመር 939 እንዲሁም በቀጥታ የስልክ መስመሮች 0111555300 ወይም በ0111568601 በመደወል ለኮሚሽኑ ማሳወቅ እንደሚችል ጠቁመዋል።

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.