ከመዲናዋ ለመሬት መንቀጥቀጥ ተጋላጭነት ጋር በተያያዘ የባለሙያዎች ግብረ-ኃይል ተዋቀረ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲስ አበባ ወደፊት ለመሬት መንቀጥቀጥ የሚኖራትን ተጋላጭነት ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ለቅድመ ጥንቃቄ የሚረዱ ጥናቶችን የሚያካሂድ የባለሙያዎች ግብረ-ኃይል ተዋቀረ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦፊዚክስ፣ ስፔስ ሳይንስና አስትሮኖሚ ተቋም እንዲሁም ከጂኦሎጂካል ሰርቬይ ምሁራን ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል፡፡
በውይይታቸውም ሰሞኑን በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ስለተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ እና ንዝረት እንዲሁም አጠቃላይ ስርጭቱን በተመለከተ መክረናል ሲሉ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡
በዚሁ ወቅት ምሁራኑ ጥናቶችን ማቅረባቸውን የገለጹት ከንቲባዋ÷ ጥናቶቹ እንደሚያሳዩት በአዲስ አበባ በአሁኑ ሰዓት በአፋር እና አካባቢው እያጋጠመን ካለው የመሬት መንቀጥቀጥ የተነሳ የመሬት ንዝረት እያጋጠመ መሆኑ ተነስቷል ብለዋል፡፡
ንዝረቱ ሲያጋጥምም መደናገጥ እና መረበሽ ሳያስፈልግ÷ በባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክረ ሐሳቦች በመከታተል መረጋጋት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
አዲስ አበባ ወደፊት ተጋላጭነት ያላት በመሆኑ ተገቢውን ጥንቃቄ ለማድረግ እና ለቅድመ ጥንቃቄ የሚረዱ ጥናቶችን ለማካሄድ የባለሙያዎች ግብረ-ኃይል በማደራጀት በጋራ ለመስራት ተስማምተናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡