Fana: At a Speed of Life!

ተደብቀው የነበሩት ነዳጅ የጫኑ ቦቴዎች…

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፋር ክልል ንግድ ቢሮ እና የክልሉ ጸጥታ አካላት ባደረጉት ርብርብ ነዳጅ ጭነው በየቦታው ተደብቀው የነበሩ ቦቴዎች ከተደበቁበት እንዲወጡ መደረጉ ተገለጸ፡፡

አዲስ አበባን ጨምሮ ለተለያዩ ክልሎች የሚጓጓዝን ነዳጅ ይዘው በአፋር ክልል ሰርዶ አድማስ በሚባል ቦታ በየጥሻው የተደበቁ ቦቴዎች በፀጥታ አካላት አሰሳ መያዛቸውን የነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን አስታውቋል፡፡

በአሁኑ ሠዓትም የክልሉ ንግድ ቢሮ ለተሽከርካሪዎቹ እጀባ እንዲሰጥ በማድረግ ወደ የመዳረሻቸው እንዲንቀሳቀሱ ተደርጓል መባሉን የባለስልጣኑ መረጃ አመላክቷል፡፡

“በወሩ መጨረሻ የነዳጅ ዋጋ ክለሳ ይሠራል” በሚል ያልተጨበጠ ተስፋ ነዳጁን ይዘው የተደበቁት እነዚህ አሽከርካሪዎች ያለአግባብ ስለሚያገኙት ትርፍ ብቻ ቅድሚያ መስጠታቸውን ባለስልጣኑ ገልጿል፡፡

በየክልል ከተሞች የነዳጅ ማደያዎችን በማድረቅ እጥረት በመፍጠር ሕብረተሰቡን የማጉላላት ሥራን መሥራታቸውንም ጠቁሟል፡፡

የፈፀሙት ሕገ-ወጥ ተግባር በተጨባጭ መረጋገጡን የገለጸው ባለስልጣኑ÷ መንግሥት ለሕብረተሰቡ ተጠቃሚነት ሲል በድጎማ የከፈለውን የነዳጅ ወጪ እንዲሸፍኑ ይደረጋል፤ ከምርት መሰወር ጋር በተያያዘም በሕግ ተጠያቂ ይደረጋሉ ብሏል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.