የመብራት ሃይል መቆራረጥ ትኩረት እንዲሰጠው ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ዘርፉ በሙሉ አቅሙ እንዲያመርት የመብራት ሃይል መቆራረጥ ትኩረት እንዲሰጠው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪ እና ማዕድን ጉዳዮች ኮሚቴ አሳስቧል።
ቋሚ ኮሚቴው ሰሞኑን በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ ቦታዎች የኢንዱስትሪ እና ማእድን ዘርፉ ያለበትን ሁኔታ አስመልክቶ የመስክ ምልከታ አካሂዷል፡፡
በምልከታው የቋሚ ኮሚቴው አስተባባሪ ሙሉቀን አድማሱ ለዓመታት የተዘጉ ኢንዱስትሪዎችን በማስከፈትና ወደምርት እንዲገቡ የማስቻል አፈፃፀሞች፣ እየተገኙ ያሉ የስራ ዕድሎች የሚበረታቱ ክንውኖች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ተተኪ ምርቶችን የማምረት ሂደቶች፤ የቴክኖሎጂ ሽግግር ማካሄድ መቻሉ፤ የሀገር ውስጥ የምርት ፍላጎትን በማዳረስ በኤክስፖርት የውጭ ምንዛሪን ከማስገኘት አኳያ እየተሰሩ ያሉ ክንውኖችንም በጥንካሬ አንስተዋል።
በሌላ በኩል ዘርፉ በሙሉ አቅሙ በማምረት ሀገራዊ የኢኮኖሚ የዕድገት ራዕይ ሙሉ በሙሉ እንዳይሳካ በክፍተትነት የሚስተዋሉ የመብራት ሃይል መቆራረጦች እንዳሉ አመላክተዋል።
ኢንዱስትሪው በሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ጥሬ ግብዓቶችን ከመጠቀም አንፃር ያሉ ውስንነቶችም በየደረጃው የሚገኙ አካላት በዘላቂነት አፋጣኝ መፍትሄ በመስጠት ሊሰራ እንደሚገባም ቋሚ ኮሚቴዉ አሳስቧል።
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የኤሌክትሪክ አገልግሎት ዳይሬክተር ተወካይ ወንድወሰን ዘመድኩን ለኢንዱስትሪና ማዕድን ዘርፉ የማይቆራረጥ ቋሚ የመብራት ኃይል አቅርቦት ከማሟላት አኳያ ልዩ ትኩረት በመስጠት ጠንካራ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የየዘርፎቹ የስራ ኃላፊዎች በተሰጠው ግብረ-መልስ መሠረት አዎንታዊ አፈፃፀሞችን በማጎልበት በክፍተት የተስተዋሉትንም በመቀበል አፋጣኝ መፍትሄ ለመስጠት፤ በዘርፉ ላይ ተጨባጭ ለውጥን ለማምጣት በትጋት በመስራት ወደ ጥራት ለመድረስ እንደሚተጉ መግለጻቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል።