የኤሌክትሪክ ብክነትን ለመቀነስ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኤሌክትሪክ ኃይል ብክነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡
የኃይል ብክነት የሚከሰተው ቴክኒካዊ እና ቴክኒካዊ ባልሆኑ ምክንያቶች መሆኑን በብሔራዊ ኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከል የኢነርጂ አካውንቲንግ እና ኳሊቲ አሹራንስ ሥራ አስኪያጅ አሸናፊ መካ ገልጸዋል፡፡
በዓለም አቀፍ የደረጃ መለኪያ አጠቃላይ ከሚመረተው ኃይል ከ5 እስከ 7 በመቶ የሚሆነው በኃይል ማስተላለፊያ ሥርዓት ላይ ሊባክን ይችላል ተብሎ እንደሚቀመጥም አስረድተዋል፡፡
ይህ ብክነት ኃይል ከማመንጨት እስከ ማከፋፈያ ጣቢያ ድረስ ባለው የኃይል ማስተላለፊያ ሥርዓት ሂደት ላይ ብቻ የሚከሰት መሆኑን ገልጸው÷ ይህም በኃይል ማሰራጫ ሥርዓት ያለውን ብክነት እንደማይጨምር አስገንዝበዋል፡፡
አሁን ላይ በኢትዮጵያ የኃይል ማስተላለፊያ ሥርዓት ውስጥ ከማመንጫ እስከ ማከፋፈያ ድረስ ባለው ሂደት በአማካይ 6 ነጥብ 8 በመቶ ብክነት አጋጥሞ እንደነበር ያለፉት ስድስት ወራት ልኬት አሳይቷል ብለዋል፡፡
በዚህም በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ ከመነጨው 13 ሺህ 435 ጊጋ ዋት ሠዓት ውስጥ 913 ጊጋ ዋት ሠዓት ያህል ኃይል ሊባክን መቻሉን አመልክተዋል።
የኤሌክትሪክ ኃይል ብክነትን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ባይቻልም መጠኑን መቀነስ እንደሚቻል ጠቅሰው÷ የኃይል ማስተላለፊያ ሥርዓት እና ዕቃዎች ባሕርይ፣ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችና ትራንስፎርመሮች ብቃት፣ ከኃይል ማመንጫ እስከ ማዕከል ያለ ርቀት እና የኃይል ከፍ እና ዝቅ ማለት የብክነት መንስዔ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልም ብክነቱን ለመቀነስ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመው÷ የፓወር ፋክተር ኮንትሮል መተግበር፣ ቶሎ ቶሎ ጥገና ማድረግ፣ ከትራንስፎርመር ዲዛይን ጋር የተያያዙ ችግሮች ማስተካከል ሥራዎችን በአብነት ጠቅሰዋል።
እንዲሁም ግሪድ ኮድ መተግበር፣ በቴክኖሎጂ መታገዝ የኃይል ጥራት ጥናት መሥራት፣ ያረጁ የኃይል መሥመሮች መቀየር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት መሆናቸውን ለፋና ዲጂታል ገልጸው÷ ብክነትን ለመቀነስ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
በዮሐንስ ደርበው