ለኢትዮጵያ ብልጽግና እንሠራለን – ከንቲባ አዳነች
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአገልግሎት አሰጣጥና የአሠራር ችግሮችን በዘላቂነት በመቅረፍ ለኢትዮጵያ ብልጽግና ተግተን እንሠራለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች “ከቃል እስከ ባሕል” በሚል መሪ ሐሳብ ለሦስት ቀናት ያካሄዱት የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ የቅድመ ጉባዔ ውይይት ተጠናቅቋል፡፡
ብልጽግና ፓርቲ ሐሳብ በማፍለቅ፣ ለሕዝብ ቃል በመግባት እና የመተግበር አፈጻጸሙ ባህል ሆኖ እንዲዘልቅ በማድረግ ረገድ በርካታ ስኬቶች ማስመዝገቡን ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡
በ1ኛ መደበኛ ጉባዔ በተገባው ቃል መሠረት የፓርቲው ኅብረ-ብሔራዊ አንድነት መጠናከሩን፣ አካታችና አብሮነትን እንዲሁም አሳታፊ የፖለቲካ ሥርዓትን በመዘርጋት ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ወቅታዊ እና ውዝፍ ፈተናዎችን በመሻገር፣ ከተማችንን የስበት ማዕከል ያደረጉ ፕሮጀክቶችንና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ያረጋገጡ ሰው ተኮር ሥራዎችን ማከናወን ችለናል ሲሉም ነው የገለጹት።
በዚህም በግንባር ቀደምትነት ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ የልማት ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል፡፡
አመራሩ በተለወጠ የሥራ ባህል የተግባርና የአስተሳሰብ አንድነቱን አጠናክሮ እንደ ሀገርም እንደከተማም ለተመዘገቡ ውጤቶች ከፍተኛውን ሚና መጫወቱን አስገንዝበዋል።
በቀጣይም የተገኙ ውጤቶችን በማላቅ እንደ ድክመት የሚነሱ የአገልግሎት አሰጣጥና የአሠራር ችግሮችን በዘላቂነት በመቅረፍ የሐሳብ ልዕልናን በብቃት እየተገበርን በሥራ አዳዲስ ባሕል እየገነባን ለኢትዮጵያ ብልጽግና ተግተን እንሠራለን ሲሉም አመላክተዋል፡፡