Fana: At a Speed of Life!

ለገና ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ እንግዶች ይጠበቃሉ- የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የገና (ልደት) በዓልን ለማክበር ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ እንግዶች እንደሚመጡ ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት ማድረጉን የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ፡፡

የአሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ወንድምነው ወዳጅ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ ስምንት ኮሚቴዎችን በማዋቀር እንደወትሮው ሁሉ ገና በላሊበላ በድምቀት እንዲከበር የሚያስችል በቂ ዝግጅት ተደርጓል፡፡

ባለፉት ዓመታት በተለያየ ምክንያት የተቀዛቀዘውን የማኅበረሰቡ የኑሮ መሠረት የሆነውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት ግለት ለመመለስ ከፌደራል እስከ ከተማ በቅንጅት ሥራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል፡፡

ይህን ተከትሎ የከተማው ነዋሪ ከ20 በሚበልጡ የዕድር ጥምረቶች ጎብኚዎች ሳይፈስኩ እንዳይመለሱ መዘጋጀቱን÷ ወጣቶችም በከተማዋ መግቢያ ሥድስት በሮች እንግዶችን እየተቀበሉ፣ እግር እያጠቡ፣ የሚበላና የሚጠጣ እያቀረቡ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

አሁን ላይ እንደወትሮው ሁሉ እንግዶች በእግር፣ በመኪና እና በአውሮፕላን በርከት ብለው ወደ ከተማዋ እየገቡ ነው ብለዋል፡፡

ሆቴሎችም አስጎብኚዎች፣ ድጋፍ ሰጭዎች፣ ንብረት ጠባቂዎች እና ሌሎች አገልግሎት ሰጭዎችም ዝግጅታቸውን አጠናቅቀው ወደ ሥራ መግባታቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች የቅዱስ ላሊበላ እና የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በጥምረት በልዩ ድምቀት በሚከበርባት ላሊበላ በአካል ተገኝተው ገናን እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.