ሊቨርፑል ታሪካዊ ተቀናቃኙ ማንቸስተር ዩናይትድን ዛሬ ይገጥማል
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ20ኛው ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ-ግብር መሪው ሊቨርፑል 14ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ማንቸስተር ዩናይትድን ዛሬ ምሽት በሜዳው አንፊልድ ሮድ ያስተናግዳል፡፡
ሊጉ በፈረንጆቹ 1992/93 የውድድር ዓመት በአዲስ መልክ ከተዋቀረ ጀምሮ 65 ጊዜ ተገናኝተው ማንቸስተር ዩናይትዶች 29 ጊዜ ሲያሸንፉ በአንፃሩ ሊቨርፑል 20 ጊዜ ድል አድርጓል፡፡ቀሪዎቹ 16 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቅቀዋል፡፡
ማንቸስተር ዩናይትዶች ባለፉት ስምንት ተከታታይ ዓመታት ወደ አንፊልድ አቅንተው አንድም ጨዋታ ማሸነፍ አልቻሉም፡፡ ዛሬ 1፡30 በሚደረገው ግጥሚያ ሁለቱም ቡድኖች በተቃራኒ የብቃት ደረጃ ላይ ሆነው የሚገናኙ ሲሆን ባለሜዳው ሊቨርፑል በቀላሉ ሊያሸንፍ እንደሚችል ብዙዎች ግምታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የምሽቱን የደርቢ ጨዋታ የ39 ዓመቱ ማይክል ኦሊቨር የመሐል ዳኛ ሆነው እንደሚመሩት የሊጉ መርሐ-ግብር ያሳያል፡፡
ትናንት 2ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አርሰናል ነጥብ መጣሉን ተከትሎ የአርነ ሽሎት ቡድን አንድ ተጫማሪ ጨዋታ እየቀረው የነጥብ ልዩነቱን ወደ ስምንት የሚያሰፋበት መልካም አጋጣሚ ተፈጥሮለታል፡፡
በዩናይትድ በኩል አምበሉ ብሩኖ ፈርናንዴሽ እና ኡራጓያዊው አማካይ ማኑዌል ኡጋርቴ ከቅጣት የሚመለሱ ሲሆን በከፍተኛ የውጤት ቀውስ ለሚገኘው የአሰልጣኝ ሩበን አሞሪም ቡድን መልካም ዜና ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡
በፕሪሚየር ሊጉ ታሪክ ሁለቱ የሰሜን ምዕራብ እንግሊዝ ግዙፍ ክለቦች በድምሩ 39 ጊዜ ዋንጫውን በማሸነፍ ደማቅ ታሪክ ያላቸው ሲሆን ዩናይትድ 20 ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ ነው፡፡
ሊቨርፑል ዘንድሮ ዋንጫውን የሚያነሳ ከሆነ 20 ጊዜ በማሸነፍ ከታሪካዊ ባላንጣው ጋር ክብረወሰኑን ይጋራል፡፡