ከባይደን ሜዳሊያ የተበረከተለት የኢትዮጵያ ባለውለታ ቦብ ጊልዶፍ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን “አሜሪካን የተሻለች ላደረጉ” ሰዎች ፕሬዚዳንታዊ የዜጎች ሜዳሊያ ሸልመዋል።
ለሲቪል ዜጎች የሚሰጠውን ሁለተኛውን ከፍተኛ የሲቪል ሜዳሊያ ከተሸለሙት 19 ተጽዕኖ ፈጣሪዎች መካከል ደግሞ ታዋቂው ሙዚቀኛ እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ቦብ ጊልዶፍ ይገኝበታል፡፡
ስለ ድሕነት አብዝቶ የሚሞግተው የሮክ ሙዚቀኛው ቦብ ጊልዶፍ ከሶስት አስርት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ የተከሰተው ረሃብ ዜጎችን ሲቀጥፍ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ጉብኝት ማድረጉ ይታወሳል።
በወቅቱ ከወርልድ ቪዥን ሰራተኞች ጋር በመሆንም በተለይ የሙዚቃ እና ድራማ ፕሮግራሞችን በመስራት በእርዳታ ካምፕ ውስጥ ለህጻናት እያቀረበ ለአንድ ወር ገደማ በኢትዮጵያ ቆይታ ያደረገ የኢትዮጵያውያን ባለውለታ ነው።
ሙዚቀኛው ወደ ኢትዮጵያ ለጉብኝት ሲመጣ ሁኔታውን ከርቀት መመልከት አልፈለገም፤ይልቁንም በየቀኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ወደሚያስተናግዱ የምግብ እና የጤና ጣቢያዎች በማምራት በሙያው አግዟል።
በወርልድ ቪዥን ድረ ገጽ ላይ በሰፈረ አንድ ጹሑፍ በወቅቱ የድርጅቱ ባልደረባ የነበረ ግለሰብ ስለ ሙዚቀኛው ሲናገር “በእነዚያ ካምፖች ውስጥ ያለው ሁኔታ አስፈሪ ነበር፣ የሚቀርበው ምግብ፣ የመኝታው ሁኔታ ድንጋጤ ውስጥ ያስገባል፤ ሙዚቀኛው ቦኖ እና ሚስቱ ሲመጡ በጣም ደንግጠው እንደነበር እርግጠኛ ነኝ” ይላል።
በወቅቱ ቦኖ የሚደንቅ ርህራሄ ያሳየበት ወቅት እንደነበርም የድርጅቱ ባልደረባ ይገልጻል። እያንዳንዱን ልጅ በመያዝ፣ በማጫወት እና እያንዳንዷን እናት በማጽናናት ጊዜውን ይጠቀምበት እንደነበርም ያስታውሳል።
ቦብ ጊልዶፍ ከፕሬዚዳንቶች፣ጠቅላይ ሚኒስትሮች እና ከሃይማኖት አባቶች ጋር እየተገናኘም ለድሆች እና ለተገለሉ ሰዎች በመሟገት ይታወቃል። በሙዚቃ ስራዎቹ ስለ በጎ አድራጎት ይቀሰቅሳል፣ ስለ ፍትህም አጥብቆ ይጠይቃል።
በጆን ኤፍ ኬኔዲ የፕሬዚዳንትነት ዘመን በተቋቋመውና በፕሬዚዳንቱ ጠቋሚነት እና በገለልተኛ አማካሪ አማካኝነት በሚሰጠው የሜዳሊያ ሽልማት ላይ ሙዚቀኞች፣ ስፖርተኞች፣ ፖለቲከኞች፣ ባለሃብቶች፣ ተዋንያን እና ሌሎችም ተሸላሚ መሆናቸውን የዋይት ሀውስ መረጃ አመላክቷል።