Fana: At a Speed of Life!

ጥበበኛ መዳፎች…

 

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ማኅበራዊ ሚዲያን ከጥፋት ድርጊቶች አፋትተው ታሪክ ሠሪዎችን በጥበብ እየዘከሩ ስላሉ አብሮ አደግ ወጣቶች ቴዎድሮስ ጌታቸው እና ቢኒያም ተዋቸው ድንቅ ሥራዎች እናጋራችሁ፡፡

በወጣቶቹ ቤት የተጣለች ቆርኪ፣ ቫዝሊን፣ ፕላስቲክ፣ ካርቶን፣ ሻማ፣ ክር እና ሌሎች ቁሶች ድምር ውጤት ባልተገመተ ሁኔታ የአንድ ታዋቂ ሰው ምስለ-ገጽ ይወልዳል፡፡

ጥበበኛ መዳፍ ያላቸው እነዚህ ጣቶች ከልጅነታቸው አንስቶ የሥዕል ሥራ ይሞክሩ እንደነበር ገልጸው÷ በዘርፉ ትልቅ ደረጃ እንደምንደርስ አጋጣሚዎች አረጋግጠውልናል ይላሉ፡፡

ምንም እንኳን በዚሁ የሥዕል ሥራ በየፊናቸው ቢጓዙም ከጊዜ በኋላ÷ ለአንድ ትልቅ ግብ በጋራ መሥራት እንዳለባቸው ተግባብተው ሥራ ከጀመሩ ሰንበትበት ማለታቸውን ያነሳሉ፡፡

ሥራዎቻቸውን ዐይተው ችሎታቸውን ከመሰከሩት የቅርብ ሰዎቻቸው ባሻገርም÷ ሥራቸው ወደ ብዙኃን እንዲደርስ ወደ ቲክቶክ መንደር መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህ የማኅበራዊ ሚዲያ አማራጭ አንዳንዶች ግጭት ለመፍጠር በሚኳትኑበት ወቅት ከፋና ዲጂታል ጋር ቆይታ ያደረጉት ወጣቶች ግን ተሰጥኦአቸውን ለበርካቶች እያደረሱ ሥራቸውን ለማሳለጥ እየተጠቀሙበት ነው፡፡

ወጣቶቹ ቲክቶክንና ሌሎች አማራጮችን ተጠቅመው ከሳሏቸው እና አድናቆትን ካተረፉባቸው ሥራዎቻቸው መካከል÷ ድምፃዊ መሐሙድ አሕመድ፣ አስቴር አወቀ ፣ ኤፍሬም ታምሩ፣ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)፣ ታምራት ደስታ፣ ዳዊት ነጋ እና ኢዮብ መኮንን ይጠቀሳሉ፡፡

በተጨማሪም አትሌት አበበ ቢቂላ፣ ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ እና ጋዜጠኛ አስፋው መሸሻ  ወጣቶቹ በሥራቸው ከፍ ካደረጓቸው መካከል ናቸው፡፡

አንድን ሥዕል ለመሥራት እስከ አራት ቀናት እንደሚፈጅባቸው፤ ሂደቱም አድካሚ ስለመሆኑ ይናገራሉ፡፡

ምንም እንኳን አብዛኞቹ ሥራዎቻቸው አድናቆት ቢያስገኙላቸውም÷ 7 ሺህ ቆርኪዎችን በመጠቀም የሠሩት የድምፃዊ ኢዮብ መኮንን ሥዕል ቀዳሚ ነው ይላሉ፡፡

ከተከታዮቻቸው አድናቆትና ማበረታቻ እየተቸራቸው መሆኑን ጠቁመው÷ ለአብነትም ከጋዜጠኛ አስፋው መሸሻ ልጅ ልብ የሚያሞቅ ድጋፍ እንደደረሳቸው ያወሳሉ፡፡

ወጣቱ በጎ ባልሆነ ነገር የተገኘ ዕውቅና ዕድሜው አጭር መሆኑን ተገንዝቦ ማኅበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ በመጠቀም ተሰጥኦውን ለብዙኃኑ ማድረስ፣ ሰውን መርዳት፣ ማደግ እና እራሱን ማሳደግ ይገባዋል ይላሉ፡፡

በጎ ሥራቸውን ማስቀጠልና ተባብረው በዘርፉ ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሰው ሀገራቸውን ማስጠራት ራዕያቸው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.