ከተረጂነት ወደ አምራችነት የተሸጋገሩ ከ31ሺህ በላይ የከተማዋ ነዋሪዎች ተመረቁ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በምግብ ዋስትና ሴፍቲኔት ፕሮግራም የስራ እድል አግኝተው ሲሰሩ የነበሩ ከተረጂነት ወደ አምራችነት የተሸጋገሩ 31ሺህ 2 የከተማዋ ነዋሪዎች ተመርቀዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ከከንቲባ አዳነች አቤቤ በተጨማሪ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራና ክህሎት ቢሮ ሃላፊ ጥራቱ በየነ፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዲሞክራሲ ስርዓት ማስተባበሪያ ፅ/ቤት ኃላፊ ሞገስ ባልቻና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል ።
በዚሁ ጊዜ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ÷ “ድህነት ብዙ ጊዜ አንገታችንን በማስደፋት ለተረጂነት አጋልጦን ቢቆይም በልቶ ለማደር ብቻ ሳይሆን የሰውነት ክብራችንን ለመጠበቅና ከእራሳችን አልፎ ሀገራችንን ለመለወጥ በሰራነው ስራ ችለን አሳይተናል” ብለዋል።
“በጅምሩ የተቀየረው የእናንተ ህይወት ብቻ ሳይሆን የከተማችንና የሀገራችንም ህልውና ነውና አሁንም ጠንክራችሁ በመስራት የተሻለውንና የበለጠውን ለውጥ እንድታሳዩ” ሲሉም ለተመራቂዎቹ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ከንቲባዋ አክለው እንደሀገር ፍትሐዊ የሀብት ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በተያዘው ዕቅድ በቀጣይ ከ154 ሺህ በላይ ዜጎች ስልጠናቸውን እንደሚጀምሩም ጠቁመዋል።
አቶ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው÷በመጀመሪያው የስልጠና ዙር 415 ሺህ 923 ዜጎች ጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመው በሁለተኛው ዙር ደግሞ ከ31 ሺህ በላይ ለሚሆኑ እማና አባዎራ ስልጠና በመስጠት 107 ሺህ 398 የቤተሰብ አባላትን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል ።
በአጠቃላይ በሴፍትኔት ስልጠና ፕሮግራሙ ከ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላይ በመመደብ ለሰልጣኞች የገንዘብ ድጋፍ በመስጠት እራሳቸውንና ሌሎችን መጥቀም እንዲችሉ ማድረግ ተችሏል ነው የተባለው።
በሰማኸኝ ንጋቱ