በጎንደር የሰዓት ገደብ እንቃስቃሴ ላይ ማሻሻያ ተደረገ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በጎንደር ከተማ የነበረው የፀጥታ ችግር መሻሻል ማሳየቱን ተከትሎ የከተማው የፀጥታ ም/ቤት በተሽከርካሪና በሰው እንቅስቃሴ ላይ ጥሎት የነበረውን የሰዓት ገደብ ማሻሻሉን አስታወቀ።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ሃላፊ ረ/ኮሚሽነር አየልኝ ታክሎ እንዳሉት ÷የከተማው የፀጥታ ም/ቤት በተሽከርካሪና በሰው እንቅስቃሴ ላይ ጥሎት የነበረውን የሰዓት ገደብ ወደ አራት ሰዓት ከፍ እንዲል ውሳኔ አሳልፏል።
የተፈቀደላቸው ባጃጆች እስከ ምሽት አራት ሰዓት መስራት እንደሚችሉ የገለጹት ረዳት ኮሚሽነሩ÷ሌሎች ባጆጆች ደግሞ በቀደመው የሰዓት ገደብ እስከ 12 ስዓት ብቻ መንቀሳቀስ እንደሚችሉ ገልጸዋል።
ከተማዋ የገናና የጥምቀት በዓልን በድምቀት እንድታከበር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመው÷ የከተማው ነዋሪም ሆነ እንግዶች በነፃነት መንቀሳቀስ እንዲችሉ ታስቦ የሰዓት ማሻሻያ መደረጉን አስረድተዋል፡፡
በከተማዋ በሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች መስታወት ላይ ጥቁር ስቲከር የለጠፉ ሁሉ እንዲያነሱ ውሳኔ መተላለፉም ተናግረዋል፡፡
ይህን በማያደርጉ አካላት ላይ የፀጥታ ሃይሉ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ነው አጽንኦት የሰጡት፡፡
የሰዓት ማሻሻያ ገደቡ ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን÷ሁሉም የተጣለውን የሰዓት ገደብ እንቅስቃሴ አክብሮ እንዲንቀሳቀስ ፖሊስ አሳስቧል፡፡
በምናለ አየነው