Fana: At a Speed of Life!

ኮሚሽኑ በ500 ሚሊየን ብር በኮምቦልቻ ያስገነባው ሕንጻ ተመረቀ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን በ500 ሚሊየን ብር ወጪ በኮምቦልቻ ከተማ ያስገነባው ዘመናዊ የቢሮ መገልገያ ሕንጻ በዛሬው ዕለት ተመርቋል፡፡

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የተገኙት የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ ÷ ኢኮኖሚው በሚያመነጨው ልክ ገቢን አሟጦ ለመሰብሰብ እየተደረገ ባለው ጥረት ውጤት እየተመዘገበ ነው ብለዋል፡፡

ለውጡ ሲጀመር በዓመት ከ200 ቢሊየን ብር በታች ገቢ ይሰበስብ የነበረው በዘንድሮው በጀት ዓመት ያለፉት አምስት ወራ ብቻ ከ380 ቢሊየን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን አመላክተዋል።

አገልግሎት አሰጣጡን በማዘመንና ገቢን በማሳደግ የህብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በየደረጃው ለመመለስ እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በሀገሪቱ የሚገኙ የጉምሩክ ቅርንጫፎችን በማጠናከርና በመደገፍ ለኢትዮጵያ ሁለተናዊ እድገት ሚናቸውን እንዲወጡ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያን ሁለተናዊ እድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ ኮሚሽኑ የድርሻውን ለመወጣት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ አሰራሩን ለማዘመን በቴክኖሎጂ የተደራጀ፣ ከወረቀት ንክኪ ነፃና ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታወቀዋል።

ይህም ኮንትሮባንድና ሌሎችንም ሕገ ወጥ አሰራሮችን በመከላከል የወጭና ገቢ እቃዎች ጤናማ የንግድ ስርዓት እንዲይዙ እንደሚያግዝ ነው ያስረዱት፡፡

በአለባቸው አባተ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.