Fana: At a Speed of Life!

አየር መንገዱ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከ20 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች ፈተና እየሰጠ ነው

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ወጣቶች የአቪዬሽን ዘርፉን እንዲቀላቀሉ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ከ20 ሺህ በላይ ለሆኑ አመልካቾች የጽሑፍ ፈተና እየሰጠ መሆኑን አስታውቋል።

ፈተናው በአዳማ፣ አምቦ፣ አርባ ምንጭ፣ አሶሳ፣ ባሕር ዳር፣ ደሴ፣ ድሬዳዋ፣ ጋምቤላ፣ ጎንደር፣ ሀዋሳ፣ ጅግጅ፣ ጅማ፣ መቐለ፣ ነቀምቴ፣ ሮቤ፣ ሰመራ፣ ወልቂጤና አዲስ አበባ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችና የፈተና ጣቢያዎች ነው እየተሰጠ የሚገኘው፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሃና አጥናፉ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷የፈተና አሰጣጥ ሒደቱ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ዘርፉን መቀላቀል የሚፈልጉ ወጣቶችን ተደራሽ ማድረግ ያስችላል፡፡

የአየር መንገዱን ዓለም አቀፍ ተመራጭነትና ተወዳዳሪነት ለማስቀጠል በሰለጠነ የሰው ኃይል ልማት ማፍራት ላይ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ብቻ ተወስኖ የቆየውን የአቪዬሺን ባለሙያዎች ምልመላ በተለያዩ አካባቢዎች በማስፋት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ነው ያስረዱት፡፡

በዛሬው ዕለትም በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ 18 ዩኒቨርሲቲዎች ከ20 ሺህ ለሚበልጡ ተወዳዳሪዎች የምልመላ ፈተና እየተሰጠ መሆኑን ሃላፊዋ ጠቅሰዋል።

አየር መንገዱ ከኢትዮጵያውያን ዜጎች በተጨማሪ በተለያዩ ውጪ ሀገራት በሚገኙ የመዳረሻ ቢሮዎች የሀገራቱን ዜጎች አወዳድሮ በመቅጠር እየሰራ እንደሚገኝም ተጠቁሟል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.