በዲጂታል አገልግሎት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) እና የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም÷ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለማፋጠን በጋራና በትብብር መሥራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት÷ የሀገር ኩራትና ምልክት የሆነው ኢትዮ ቴሌኮም በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ግንባር ቀደም ሚና በመጫወት እንዲሁም በዲጂታል አገልግሎቶችና ቴሌብር አስደማሚ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የዲጂታል አገልግሎት ተደራሽነትና አካታችነት በመጨመር ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በትብብር እንደሚሰራ አስገንዝበዋል፡፡
በዚህም በኢገቨርመንት፣ ኢኮሜርስ፣ ኢኖቬሽን፣ በጀማሪ የሥራ ፈጠራ፣ ጥናትና ምርምር፣ ስማርት ስልክ ስርጸትና የዲጂታል ክህሎትን ለመሻሻል በቅንጅት እንሰራለን ብለዋል፡፡
ፍሬሕይወት ታምሩ በበኩላቸው÷ ኢትዮ ቴሌኮም የዲጂታል ኢትዮጵያን ጉዞ ለማሳካት እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባራትን አስረድተዋል፡፡
ተቋማቱ የዲጂታል ኢትዮጵያ ትራንስፎርሜሽን ለማፋጠን ቋሚ የጋራ መድረክ በመፍጠር የዜጎችን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ ጉዳዮች ላይ በቅርበት ለመሥራት መወሰናቸው ተገልጿል፡፡
በለጠ ሞላ (ዶ/ር) የኢትዮ ቴሌኮምን ኤክስፒሪየንስ ማዕከል ጎበኙ ሲሆን÷ በዚህም የስማርት ሲቲ ፕሮጀክትን ጨምሮ እንደ ግብርና፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ኢንዱስትሪና ሌሎች ዘርፎችን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ግዙፍ አቅም መገንባቱን አረጋግጠዋል፡፡