ሁዋጂያን በድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጣና በኢንቨስትመንት ልማት ላይ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳለው ገለፀ
ታሕሣሥ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የተለያዩ ቆዳ ጫማዎችን በማምረት ታዋቂ የሆነው የቻይናው ሁዋጂያን ግሩፕ በድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጣና በኢንቨስትመንት ልማት ላይ የመሰማራት ፍላጎት እንዳለው ገልጿል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) ከሁዋጂያን ኢትዮጵያ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሚስተር ሁአ ሮንግ ዣንግ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ ዋና ስራ አስፈፃሚው÷ ሁዋጂያን ግሩፕ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት በማንቀሳቀስና ለወጣቶች የስራ እድልን በመፍጠር በእውቀትና ክህሎት ሽግግር ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
ኩባንያው በቀጣይ በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ላይ በሚያከናውናቸው ኢንቨስትመንት ስራዎች ኮርፖሬሽኑ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡
ሚስተር ሁአ ሮንግ ዣንግ በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ውስጥ ሰፊ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸው፣ አሁን ላይም በነጻ ንግድ ቀጣናው ገብተው ለመስራት መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል፡፡
ሁዋጅያን ኢትዮጵያ ኩባንያ በፈረንጆቹ 2015 ጀምሮ እየሰራ ያለ ኩባንያ ሲሆን አሁን ላይ ከ150 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ ኢንቨስትመንት በማንቀሳቀስ፤ ከ12 ሺህ በላይ የስራ እድል መፈጠሩን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡