Fana: At a Speed of Life!

የጎዴ የተቀናጀ አርብቶ አደሮች መንደር በሌሎች አካባቢዎች እንደ ሞዴል ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል – አቶ አህመድ ሽዴ

አዲስ አበባ፣ ታህሣሥ 26/2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሶማሊ ክልል የተገነባው የጎዴ የተቀናጀ አርብቶ አደሮች መንደር በሌሎች የአርብቶ አደር አከባቢዎች እንደ ሞዴል ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ገለፁ፡፡

ሚኒስትሩ በፌዴራል መንግስት እና በሶማሊ ክልል መንግስት የተገነባውን የጎዴ የተቀናጀ አርብቶ አደሮች መንደር በጎበኙበት ወቅት እንደተናገሩት÷ መንደሩ ለአርብቶ አደር ማህበረሰብ እንደ ማስተማሪያ የሚያገለግል ነው ብለዋል፡፡

የተቀናጄ የአርበቶ አደሮች መንደር አርብቶ አደሮች የእንስሳት ተዋፅኦ ምርታቸውን በጋራ ለማቀነባበር የሚያስችል፣ የመብራት፣ የውሃ እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች የተሟሉለት መንደር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ በፊት የተገነቡ የአርበቶ አደሮች መንደር ዝናብን መቋቋም የማይችሉ እና ለተለያዩ ተፈጥሯዊ ችግሮች ተጋላጭ የነበሩ መሆናቸውን ያስታወሱት ሚኒስትሩ÷ በጎዴ የተገነባው የተቀናጄ የአርብቶ አደሮች መንደር ይህን ችግር የሚቀርፍ ነው ብለዋል፡፡

እነዚህ መንደሮች በሌሎች አርብቶ አደር አካባቢዎች እንደ ሞዴል ሊወሰዱ እንደሚገባ እና የክልሉ መንግስት የአርብቶ አደር መንደሮች በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ እንዲሆኑ ሊያበረታታ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የሶማሊ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሙሰጠፌ መሀመድ በበኩላቸው÷ የጎዴ የተቀናጄ የአርብቶ አደሮች መንደር አርበቶ አደሩ ከተሜነትን እንዲለማመድ እና ኑሮውን እንዲያዘምን የሚያግዝ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አርብቶ አደሮች የአኗኗር ባህላቸው ተንቀሳቀሽ እንደነበር እና በዚህም ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ እንደነበሩ ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳደሩ÷ መንደሩ አርብቶ አደሮች ወደ ከተማ በመጠጋት የመሰረተ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

አርብቶ አደሮች ከእንስሳት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንጂ ከከተሜነት ሊርቁ እንደማይገባ በመግለፅ የክልሉ አርበቶ አደሮች የትምህርት፣ የጤና እና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን በማግኘት ኑሯቸውን ሊያዘምኑ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በቀጣይም የክልሉ መንግስት አርበቶ አደሩን ከከተሜነት ጋር ለመማስታረቅ የአርበቶ አደሮችን መንደሮችን በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ አመላክተዋል፡፡

የተቀናጀ የአርብቶ አደር መንደሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጉብኝት አድርገዋል።

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.