የእሳተ ገሞራ ምልክት የሆነው የዱለቻ አካባቢ ፍንዳታ ጥንቃቄ እንደሚፈልግ ተጠቆመ
አዲስ አበባ፣ ታህሣሥ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፋር ክልል ገቢ ረሱል ዞን ዱለቻና አካባቢው የተከሰተው ፍንዳታ የእሳተ ገሞራ ምልክት በመሆኑ አስፈላጊው ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አሳሰበ፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስነ ምድር ትምህርት ክፍል መምህር እና ተመራማሪ ገዛኸኝ ይርጉ (ፕ/ር) ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንደተናገሩት፤ በዱለቻ እና አካባቢው ትናንት የተከሰቱት ፍንዳታዎች እሳተ ገሞራ ሊኖር እንደሚችል ማሳያ ምልክቶች ናቸው፡፡
በፍንዳታው የተስተዋለው ከፍተኛ ጭስ እና ቅሪትም ከታች ወደ ላይ እየገፋ የመጣ ቅልጥ ዐለት ስለመኖሩ እንደሚያሳዩ ተናግረዋል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎችን ከጉዳዩ አሳሳቢነት አንጻር ወደ ሌላ አካባቢ የማዘዋወር ስራ በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ጉዳዩን በንቃት እየተከታተለው መሆኑን ገልጸው፤ ወቅታዊ መረጃዎችንም እየተከታተለ እንደሚያደርስ አረጋግጠዋል፡፡
በሰለሞን ይታየው