Fana: At a Speed of Life!

አፕል ኩባንያ በተጠቃሚዎቹ ለተከፈተበት ክስ 95 ሚሊየን ዶላር ለመክፈል ተስማማ

አዲስ አበባ፣ ታህሣሥ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አፕል ኩባንያ የአይፎንና የአፕል ሰዓት ተጠቃሚ ደንበኞቹ በፈረንጆቹ 2019 ለመሰረቱበት ክስ 95 ሚሊየን ዶላር ካሳ ለመክፈል መስማማቱ ተገለጸ።

ደንበኞቹ ግዙፉን የስልክ አምራች ኩባንያ የከሰሱት ሲሪ በተባለ በድምፅ የሚታዘዝ አገልግሎት መስጫ ሶፍትዌር በኩል የግል መረጃዎቻችንን ያለ ፈቃድ ቀድቶ ለሶስተኛ ወገን አስተላልፏል በሚል ነው።

ኩባንያው በሲሪ አማካኝነት የተጠቃሚዎችን ንግግር ሳያውቁና ሳይፈቅዱ በመቅዳት ለማስታወቂያ ድርጅቶችና ለሶስተኛ ወገን አሳልፎ ሰጥቷል በሚል ነው በሰሜን ካሊፎርኒያ ኦክላንድ ግዛት ፍርድ ቤት ክስ የቀረበበት።

ኩባንያው ሲሪ አገልግሎት የሚሰጠው በተጠቃሚው ጥያቄ መሰረት ብቻ መሆኑን ቢያስታውቅም፤ ሰዎች የድምፅ እገዛ ሳይጠየቁ የሚያደርጓቸውን ንግግሮችና የሚያነሷቸውን ርዕሰ ጉዳዮች እየቀረጸ ወደ ኩባንያው በመላክ ለማስታወቂያ ድርጅቶችና ሶስተኛ ወገን አሳልፎ በመስጠት ነው ክስ የተመሰረተበት።

ድርጅቱን ከከሰሱት ደንበኞች አንዱ ሁኔታውን ሲያስረዳ ከሃኪሜ ጋር ስለ ቀዶ ህክምና መወያየቴን ተከትሎ ከህክምና አገልግሎት ድርጅቶች ጉዳዩን የተመለከቱ ማስታወቂያዎች ተላኩልኝ ብሏል።

ሌላዋ ከሳሽ ደግሞ ልጄ ኤየር ጆርዳን ስለተባለ ጫማ ስታወራ ንግግሯ ተቀርጾ በአፕል በይነ-መረብ በኩል ተከታታይ የጫማ ማስታወቂያ ተልኮላታል ብለዋል።

ክሱን የመሰረቱት በፈረንጆቹ ከመስከረም 17 ቀን 2014 እስከ 2024 ድረስ ባለው ጊዜ የድርጅቱን ምርት ሲጠቀሙ የነበሩ ደንበኞች መሆናቸውን ዩፒአይ ዘግቧል።

የኩባንያው ሃላፊዎች ከፈረንጆቹ 2019 በፊት የተቀረጹ ድምጾችን ለመሰረዝ የተስማሙ ሲሆን ደንበኞች መረጃቸውን ለሲሪ ለማጋራት ይሁንታን የሚጠይቅ አሰራር ለማካተት ማሰባቸው ተገልጿል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.