ክልሉ ከቱሪዝም የማገኘውን ጥቅም ለማሳደግ እየሠራሁ ነው አለ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የመስኅብ ሥፍራዎችን በመጠበቅ እና በመንከባከብ ከዘርፉ በይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን በትኩረት እየሠራ መሆኑን የአፋር ክልል ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡
ከሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ 1 ሺህ 548 የውጭ እና 241 ሺህ የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ክልሉን መጎብኘታቸውን የቢሮው ምክትል ኃላፊ አብዱ መሐመድ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡
ከውጭ እና ከሀገር ውስጥ ጎብኝዎችም በአጠቃላይ 726 ሚሊየን 97 ሺህ 803 ብር መገኘቱን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም በዘርፉ በተለያዩ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት በኩል 60 ሚሊየን ብር በክልሉ ኢኮኖሚ ላይ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አንስተዋል፡፡
ክልሉ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት መስጠቱን ገልጸው÷ በውጭ እና በሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ቁጥር እንዲሁም በተገኘ ገቢ መጠን ዘንድሮ ከፍተኛ ዕድገት ታይቷል ብለዋል፡፡
ለ320 ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩን፣ ለጎብኚዎች በይበልጥ የተሻለ አገልግሎት ለመሥጠትም ምቹ የእንግዳ ማረፊያን ጨምሮ የቱሪዝም ኢንቨስትመንት አሠራሮችን በማጠናከር፣ የማበረታቻ አሰጥጥ ሥርዓት እየተተገበረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በክልሉ የሚገኙ ነባር እና አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎች ላይ እሴት የሚጨምር ሥራ መከናወኑንም አንስተዋል፡፡
ለአብነትም የኤርታ-ኣሌ መንገድ ዲዛይን ሥራ ተሠርቶ በቀጣይ ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋራ በመተባበር ወደ ሥራ ለመግባት ቅድመ ዝግጅት ተጠናቅቋል ነው ያሉት፡፡
በዮሐንስ ደርበው