Fana: At a Speed of Life!

ለበዓሉ የግብዓት አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት በቂ ዝግጅት ተደርጓል

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በመዲናዋ የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ የምርት አቅርቦት ችግር እንዳይፈጠር በቂ ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታወቀ፡፡

በቢሮው የገበያ መረጃ ጥናትና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር ሰማ ጀማል ከፋና ዲጂታል ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት÷ የንግድ ቢሮ ከበዓሉ ጋር በተያያዘ ሊፈጠር የሚችለውን የምርት እጥረትና የዋጋ ንረት ለመከላከል ግብረ ሃይል አቋቁሞ የክትትልና የቁጥጥር ስራ እየሰራ ነው፡፡

በዚህም በከተማው በሚገኙ ሶስት ትልልቅ የገበያ ማዕከላት እና በየክፍለ ከተሞች በሚገኙ የገበያ ቦታዎች በሰብል፣ በኢንዱስትሪና በሌሎች ምርቶች ላይ ሰፊ የግብዓት አቅርቦት እንዲኖር መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ለበዓሉ በስፋት በግብዓትነት በሚውሉ የዘይት፣ የስኳር እና በሌሎች ምርቶች ላይ እጥረት እንዳይከሰት ከሚመለከታቸው ተቋማትና ክልሎች ጋር በመሰራቱ ለበዓሉ ምንም አይነት እጥረት እንደማይኖር አረጋግጠዋል፡፡

በሁሉም የገበያ ማዕከላት የበዓል ግብዓቶች ከ15 እስከ 20 በመቶ ቅናሽ በማድረግ ለተጠቃሚው እየቀረበ መሆኑን አንስተው÷ ይህም እስከ ፊታችን ታሕሣሥ 28 እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

ምርት በሚደብቁና ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረት እንዲፈጠር በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይም እርምጃ እየተወሰደ ስለመሆኑ ጠቁመዋል፡፡

በአመለወርቅ ደምሰው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.