Fana: At a Speed of Life!

ሚድሮክ በ26 ቢሊየን ብር ወጪ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የወርቅ ፋብሪካ ሊገነባ ነው

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሚድሮክ ኢንቨትመንት ግሩፕ በ26 ቢሊየን ብር ወጪ በቤንሻንጉል ክልል መተከል ዞን ቡለን ወረዳ የወርቅ ማዕድን ፋብሪካ ሊገነባ መሆኑን አስታወቀ።

ሚድሮክ ፋብሪካውን ለመገንባት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በግልገል በለስ ከተማ መክሯል።

የሚድሮክ የማዕድን ዘርፍ ኮርፖሬት ፕሮጀክት ዳይሬክተር ሱራፌል ላቀው፥ ድርጅታቸው የወርቅ ማዕድንን ዘመናዊ በሆነ መንገድ ለማውጣትና ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በቡለን ወረዳ ፋብሪካውን ለመገንባት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ፋብሪካው ከ1 ሺህ 500 በላይ የስራ እድል እንደሚፈጥር ጠቁመው፤ የፋብሪካው መገንባት በዘርፉ ያለው ሃብት እንዳይባክን እንደሚያደርግ እና ህገ-ወጥ የወርቅ ዝውውርን መልክ በማስያዝ ለሀገር ጥቅም እንዲውል እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

የክልሉ ማዕድን ቢሮ ሃላፊ አቶ አድማሱ ሞርካ፥ ክልሉ የማዕድን ሃብቱን አቅም ባላቸው ኩባንያዎችና ባለሃብቶች በዘመናዊ ቴክኖሎጂና ዕውቀት በመታገዝ እንዲለማ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የፋብሪካው መገንባት የአካባቢውን ኢኮኖሚ እንደሚያነቃቃ እና እንደ ሀገር ያለውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ ዓይነተኛ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አትንኩት ሽቱ በበኩላቸው፥ ፋብሪካው በዕቅዱ መሰረት እንዲከናወን በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.