ዕድገትና ብልፅግና ለማሳካት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል – ወ/ሮ ዓለሚቱ ኡሞድ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጋምቤላ ክልልን ሁለንተናዊ ዕድገትና ብልፅግና ለማረጋገጥ የተቀመጡ ግቦች እንዲሳኩ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል ሲሉ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።
በሰላም ሚኒስቴርና በክልሉ መንግስት የጋራ ትብብር ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ህዝባዊ የሰላም ኮንፍረንስ ሲጠናቀቅ ርዕሰ መስተዳድሯ ባስተላለፉት መልዕክት÷ ያለ ህብረተሰቡ ተሳትፎ የትኛውም ልማት ውጤታማ ሊሆን አይችልም።
በመሆኑም ለክልሉ ሁለንተናዊ ዕድገትና ብልፅግና መሳካት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ሮን (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ በክልሉ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
የኮንፍረንሱ ተሳታፊዎች ባወጡት የአቋም መግለጫ አንድነታችንና አብሮነታችንን በማጠናከር ለዘላቂ ሰላምና ልማት ተግተን እንሰራለን ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡