Fana: At a Speed of Life!

ኢቢሲ ወደ ተሻለ ምዕራፍ እንዲሸጋገር አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል – ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) አሁን ካለው ደረጃ ወደ ተሻለ ምዕራፍ እንዲሸጋገር አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ሸጎሌ የሚገኘውን የኢቢሲ ዋና መሥሪያ ቤት መጎብኘታቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ አስታውቀዋል፡፡

ኢቢሲ የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ባህልና ማህበራዊ እሴቶች በማስተዋወቅ እና ለመልካም ገፅታ ግንባታ እያደረገ ያለው ጥረት ለሌሎች መገናኛ ብዙኃን ምሳሌ መሆን የሚችል ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ተቋሙ ዘመኑን የዋጀ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ከመገንባት ባሻገር “ወደ ይዘት” በሚል መሪ ቃል በጀመረው የይዘትና የአቀራረብ ማሻሻያ ተደራሽነቱን ለማስፋት እየሠራቸው የሚገኙ ተግባራት አበረታች እንደሆኑ ጠቅሰዋል።

ኢቢሲ በተለያዩ ክልሎች አዳዲስ ስቱዲዮዎችን ገንብቶ ወደ ሥራ ማስገባቱ የኢትዮጵያን አዎንታዊ መልክ ለማጉላትና የወል ትርክትን ለመገንባት ከፍተኛ አስተዋጽዖ አለውም ነው ያሉት፡፡

ተቋሙ ተአማኒና ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ ለመሆን፣ የሀገርን ታሪክና ባህል ለማስከበር እና ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲፈጠር፤ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ አሁን ካለው ደረጃ ወደ ተሻለ ምእራፍ እንዲሸጋገር መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ሲሉም አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.