Fana: At a Speed of Life!

8 የመንግሥት ልማት ድርጅቶች የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግን ተቀላቀሉ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ስምንት ተጨማሪ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግን በይፋ ተቀላቅለዋል።

ድርጅቶቹም የኢትዮ ፖስታ፣ ኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ፣ የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት መሆናቸው ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ስራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ በስሩ 40 የልማት ድርጅቶችን በባለቤትነት እያስተዳደረ መሆኑን ገልጸዋል።

ድርጀቱ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን የኮርፖሬት አስተዳደርና ትርፋማነት በማሻሻል የተሳካ ስራ እያከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተጨማሪም የሀገር ሀብት ከሀገር ዕዳ ይበልጣል የሚል መርህ እንዳለው ጠቅሰው፥ ለዚህም የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ያላቸውን ሀብት አውቆ፣ በአግባቡ ማስተዳደርና ለሀገር ጥቅም ለማዋል በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የቦርድ አባል እና የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ፤ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ገቢ በማመንጨት፣ የመሰረተ ልማት በመገንባትና በስራ ዕድል ፈጠራ ትልቅ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።

በሀገር እና በዓለም አቀፍ አውድ ውስጥ ተወዳዳሪ፣ ትርፋማና ቀጣይነት ያለው የቢዝነስ ስራን ለማሳለጥ የልማት ድርጅቶቹ በአሰራር፣ በተቋማዊ አደረጃጀትና በፖሊሲ ጠንካራ መሆን እንዳለባቸውም መጠቆማቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.