ከሆርቲካልቸር ወጪ ንግድ ከ216 ሚሊየን በላይ ዶላር ገቢ ተገኘ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት አምስት ወራት ከሆርቲካልቸር ዘርፍ ወጪ ንግድ 216 ሚሊየን 655 ሺ 430 የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ ባለፉት 5 ወራት 45 ሺህ 878 ቶን አበባ በመላክ 186 ሚሊየን 361 ዶላር መገኘቱን ገልጿል፡፡
አፈፃጸሙ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት በመጠን የ0 ነጥብ 79 በመቶ፤ በገቢ ደግሞ የ0 ነጥብ 86 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ተብሏል፡፡
በተመሳሳይ 121 ሺህ ቶን በላይ አትክልትና ፍራፍሬ በመላክ 30 ሚሊየን 294 ሺህ ዶላር የተገኘ ሲሆን÷ ገቢው ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸር የ6 ነጥብ 55 በመቶ እድገት ማሳየቱን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡
በአምስት ወራቱ የአፈፃጸም ወቅት ኔዘርላንድስ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ እና ዩናይትድ ኪንግደም እንደቅደም ተከተላቸው ከአበባ መዳረሻ ሀገራት ውስጥ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃን የያዙ መዳረሻዎች መሆናቸው ተመላክቷል፡፡
ምርጥ ሦስት የአትክልት ኤክስፖርት መዳረሻ ሀገራት ደግሞ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ እና ኔዘርላንድስ መሆናቸው ነው የተጠቀሰው፡፡
ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ጅቡቲ እና ሶማሊያ ደግሞ እንደቅደም ተከተላቸው በፍራፍሬ መዳረሻነት ከ1 እስከ 3ኛ ደረጃን የያዙ ሀገራት መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡