የበዓል ፍጆታ ምርቶችን ለገበያ ለማቅረብ በቂ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በቀጣይ በሚከበሩት የገና እና ጥምቀት በዓላት ፍጆታ የሚውሉ ምርቶችን ለህብረተሠቡ ለማቅረብ በቂ ዝግጅት መደረጉን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በሚኒስቴሩ የሀገር ውስጥ ንግድና ሸማቾች ጥበቃ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ሊቁ እንደገለፁት÷በመጪው የገናና የጥምቀት በዓላት የሠብልና አትክልት ምርቶችን ፣ የቁም እንስሳትን፣ የእንስሳት ተዋፅኦ ምርቶችን እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡
ምርቶቹን በቅዳሜና እሁድ ገበያ፣ በህብረት ስራ ማህበራት፣ በዩኒየኖች፣ ባዛሮችና መሠል የግብይት አማራጮችን በመጠቀም ያለ ምንም ዋጋ ጭማሪ ለህብረተሠቡ ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም ገልፀዋል፡፡
ከበዓላት ወቅት ጋር በተያያዘ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ በተጨማሪም ባዕድ ነገሮችን ከምግብ ምርቶች ጋር ቀላቅለው ለገበያ የሚያቀርቡ ነጋዴዎች ላይ ቁጥጥር እንደሚደረግም አስገንዝበዋል፡፡
በተጨማሪም በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች ላይ የሚገኙ የቅዳሜና እሁድ ገበያ ማዕከላት እስከ በዓሉ ዕለት ድረስ ለህብረተሠቡ አገልግሎት እየሠጡ የሚቆዩ መሆኑንም መሪ ስራ አስፈፃሚው ተናግረዋል፡፡
የተረጋጋ ገበያ እንዲኖር የሚያስችል በቂ የምርት አቅርቦት መኖሩንም በመግለጽ ነጋዴዎች ምርቶችን በመደበኛው ዋጋ እንዲያቀርቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡