50 በመቶ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በቻይና ባለሀብቶች መልማቱ ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት አምስት አመታት በኢትዮጵያ ከተጀመሩ አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች 50 በመቶ የሚሆኑት በቻይና ባለሀብቶች የለሙ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለፀ፡፡
ኮሚሽኑ ከቻይና ንግድ ምክር ቤት እና ከቻይና ኢምባሲ ጋር የቻይና ባለሀብቶችን ማበረታታት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርጓል፡፡
በውይይቱ ለቻይና ባለሀብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢን ለመፍጠር እና ተጨማሪ ባለሀበቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በዚህ ወቅት ቻይና በኢትዮጵያ ካሉ አጠቃላይ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንቶች ቀዳሚውን ስፍራ መያዟ ተገልጿል።
አሁን ላይ ቻይና በኢትዮጵያ ከ 3 ሺህ 300 በላይ ፕሮጀከቶችን እያለማች ትገኛለች ተብሏል፡፡
በዚህም ቻይና በኢትዮጵያ ከ325 ሺህ በላይ የስራ እድሎች እንዲፈጠሩ ማድረጓ ተጠቁሟል፡፡
በኢትዮጵያ ካለው አጠቃላይ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የቻይና ድርሻ 50 በመቶ መሆኑንም የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል።