Fana: At a Speed of Life!

ቲካድ ለአፍሪካ ጃፓን ግንኙነት ወሳኝ በመሆኑ ኢትዮጵያ ድጋፏን ትቀጥላለች – ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቶኪዮ ዓለም አቀፍ የአፍሪካ ኮንፈረንስ (ቲካድ) ለአፍሪካ ጃፓን ግንኙነት ወሳኝ መድረክ በመሆኑ ኢትዮጵያ ድጋፏን ትቀጥላለች ሲሉ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ ጋር ተወያይተዋል።

ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በውይይቱ ላይ እንዳሉት፤ የኢትዮ-ጃፓን ግንኙነት አንድ ክፍለ ዘመን ያስቆጠረ እና ታሪካዊ ነው።

ይህንን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗን ጠቅሰዋል።

ጃፓን በኢኮኖሚ ልማት እና በቴክኒክ ትብብር ትርጉም ያለው ድጋፍ ስታደርግ መቆየቷን ገልጸው፤ በተለይ በአሁኑ ወቅት የቀድሞ ታጣቂዎችን ወደ ማኀበረሰቡ እንዲቀላቀሉ የሚደረገውን እንቅስቃሴ፣ ለመልሶ ግንባታ እና መልሶ ማቋቋሚያ ሥራዎች የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንድትቀጥል ጠይቀዋል።

በአሁኑ ወቅት እየተተገበረ ያለው ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድል የፈጠረ በመሆኑ የጃፓን ኩባንያዎች እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል።

የቶኪዮ ዓለም አቀፍ የአፍሪካ ኮንፈረንስ (ቲካድ) ለአፍሪካ ጃፓን ግንኙነት ወሳኝ መድረክ በመሆኑ ኢትዮጵያ ድጋፏን እንደምትቀጥል ማረጋገጣቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።

አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ በበኩላቸው የኢትዮጵያ እና ጃፓን ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር እንደሚሠሩ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላም እና ፀጥታ ለማስፈን የምትሠራውን ሥራ ሀገራቸው እንደምትደግፍ ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.