Fana: At a Speed of Life!

ለበዓል ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች ላይ የጥራት ቁጥጥር እየተደረገ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ለገና በዓል ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ጥራትና ደህንነት ለማረጋገጥ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

የገናን በዓል ጨምሮ በበዓላት ወቅት የፍጆታ ሸቀጦችና ምርቶች በከፍተኛ መጠን ለገበያ የሚቀርቡበትና ሰፊ ግብይት ይደረጋል።

የባለስልጣኑ የምግብ ኢንስፔክሽንና ህግ ማስፈጸም መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ሙላቱ ተስፋዬ እንዳሉት÷ ለበዓል ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ጥራትና ደህንነት ለማረጋገጥ የተጠናከረ የክትትልና ቁጥጥር ስራ እየተከናወነ ነው።

ሰፊ ግብይት በሚፈጸምባቸው አካባቢዎች በተለይም በምግብና ምግብ ነክ ምርቶች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የጥራት ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ሸማቹ ህብረተሰቡም በግብይት ወቅት የምርቶች ጥራትና የአገልግሎት ማብቂያ ጊዜን በጥንቃቄ አጣርቶ መሸመት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

ዜጎች በግብይት ወቅት አጠራጣሪ ነገሮች ሲመለከቱም በባለስልጣኑ ነፃ የስልክ መስመር 8482 ወይም ለጸጥታ አካላት ጥቆማ እንዲሰጡ ጥሪ ቀርቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.