ኤሎን መስክ የቴስላ ሳይበር መኪና ፍንዳታ የሽብር ተግባር ሊሆን እንደሚችል ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በላስ ቬጋስ ትራምፕ ሆቴል መግቢያ በር በቴስላ ሳይበር መኪና ላይ የተከሰተው ፍንዳታ የሽብር ተግባር ሊሆን እንደሚችል የዓለም ቁጥር አንድ ቱጃሩ ታዋቂው ባለሃብት ኤሎን መስክ ገለጸ፡፡
ትናንት በፈረንጆቹ አዲስ አመት የመጀመሪያ ቀን የተመራጩ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ንብረት በሆነው ላስ ቬጋስ ትራምፕ ሆቴል መግቢያ በተከሰተ ፍንዳታ አንድ ሰው ሲሞት ሰባት ሰዎች ተጎድተዋል።
ይህንን ተከትሎ የቴስላ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኤሎን መስክ አደጋው በኒው ኦርሊያንስ የመኪና አደጋ እና በኒው ዮርክ ከተከሰው የጅምላ ተኩስ ጥቃትጋር የተያያዘ የሽብር ተግባር ሊሆን እንደሚችል ኤክስ ላይ ባሰፈረው መልእክት አስታውቋል።
የፍንዳታው መንስኤ መኪናው ነው የሚለውን ሀሳብ የተቃወመው ኤሎን መስክ፤ በፍንዳታው ጊዜ ተሽከርካሪው ምንም አይነት ችግር እንዳልነበረበት አስገንዝቧል።
መኪናው የፍንዳታ አደጋ ሲያጋጥመው ውስጥ የነበረው ሾፌር ህይወቱ ያለፈ ሲሆን፤ በውስጡ ርችቶች እና ቦምብ ይዞ ነበር ተብሏል።
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ምሽት ላይ ባደረጉት ንግግር ኋይት ሃውስ ጉዳዩን እየተከታተለ መሆኑን ገልጸው፤ የህግ አስከባሪ አካላት በኒው ኦርሊያንስ ከተፈጸመው ጥቃት ጋር ግንኙነት ስለመኖሩ እየመረመሩ ነው ሲሉ አስረድተዋል።
የፈረንጆቹ 2025 በገባ በመጀመሪያው ቀን በኒው ኦርሊያንስ በተፈጸመ የመኪና ጥቃት 15 ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍ 35 የሚሆኑ ደግሞ ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑ ይታወቃል።
በተመሳሳይ በኒው ዮርክ የምሽት መዝናኛ በአሉን በማክበር ላይ በነበሩ ሰዎች ላይ በተከፈተ የተኩስ ጥቃት 10 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።