ዲጂታል ሙስና አሳሳቢ መሆኑ ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በዲጂታል አሰራርን በመጠቀም የሚፈጸመው የሙስና ድርጊት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን የፌዴራል የሥነ-ምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።
በኮሚሽኑ የዲጂታል ሙስና መረጃ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን በላይነህ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፤ የዲጂታል አሰራርን በመጠቀም ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት ወይም ድርጊቱን ለመፈጸም የሚደረግ ሙከራ ዲጂታል ሙስና ይባላል።
ድርጊቱ የዲጂታል ስርዓቶችን በመጠቀም መረጃን ማጥፋት እና አሻሽሎ መጠቀምን ያካትታል ሲሉም አብራርተዋል።
አሰራሮችን ለማቀላጠፍ የሚተገበሩ የዲጂታል ስርዓቶችን ባልተገባ መንገድ ለግል ጥቅም የማዋል ዝንባሌ እየተስተዋለ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዲጂታል ሙስና አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ሕገወጥ የገንዘብ ማስተላለፍን ለመከላከል የሕግ ማዕቀፎች አሏት ያሉት አቶ መስፍን፤ የባንኮችን ዲጂታል የገንዘብ ማስተላለፊያ ዘዴዎች በመጠቀም ጉዳይ ለማስፈጸም የሚፈጸሙ የዲጂታል ሙስና ድርጊት መከላከል እንደሚቻል ተናግረዋል።
ምንጩ ያልታወቀ ገንዘብ ሲተላለፍ እንደ ፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ያሉ ተቋማት መሰል ጉዳዮችን በመለየት እርምጃ ይወስዳሉ ብለዋል።
ባንኮች ሕገ-ወጥ ገንዘብ ልዉዉጥ ሲከሰቱ ከእነዚህ ተቋማት ጋር አብረው መስራት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
የበርካታ ተቋማት የአገልግሎት አሠራሮች ዲጂታላይዝድ እየሆነ መምጣቱን አንስተው፤ ለዲጂታል ሙስና ተጋላጭ እንዳይሆኑ ተገቢውን ክትትል ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
እንግዳ የሆነ አሰራር ሲፈጠር ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ኮሚሽኑ ሙስናን ለመከላከል የዜጎችን ተሳትፎ ለማጠናከር ተግባራዊ ባደረገው “ኤንሲአርኤስ” የተሰኘ መተግበሪያ መጠቆምና መከታተል እንደሚቻል አስገንዝበዋል።
በደበላ ታደሰ