ባንኩ የደንበኞች አገልግሎት ንቅናቄን አስጀመረ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ “የላቀ አገልግሎት ደስተኛ ደንበኛ” በሚል መሪ ሃሳብ ለአንድ ወር የሚቆይ የደንበኞች አገልግሎት ወር በይፋ አስጀምሯል።
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ እና የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ፣ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ እና የባንኩ ከፍተኛ አመራሮችና ሰራተኞች ተገኝተዋል።
ከታህሳስ 24 እስከ ጥር 25 ለአንድ ወር በሚቆየው በዚህ መርሐ ግብር በባንኩ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ከደንበኞች ጋር ውይይት፣ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ አወደ ርዕይ እና ለደንበኞች ምስጋና የሚቀርብበት መሆኑን ተገልጿል።
አቶ አህመድ ሽዴ በዚህ ወቅት ÷ደንበኞች ለባንኩ እምነት ሰጥተው አብረው በትብብር በመስራታቸው ምስጋና አቅርበዋል፡፡
“የሕልውናችን ማዕከል መሆናችሁን ስለምናምን በቁርጠኝነት ልናገለግላችሁ ሁሌም ዝግጁ ነን” ማለታቸውንም የባንኩ መረጃ ያመለክታል።
አቶ አቤ ሳኖ በበኩላቸው ÷”ደንበኞቻችን ስለምትተማመኑብን እጅግ እናመሰግናለን ፤ባንካችን ለደረሰበት ስኬት ላደረጋችሁት አስተዋፅኦ ሁሉ ክብር ይገባችኋል” ብለዋል፡፡
ባንኩ ለደንበኞች አስተማማኝና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ሁሌም ዝግጁ እንደሆነም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡